ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 44:7-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. እስቲ እንደ እኔ ማን አለ? ይናገር፤ሕዝቤን ከጥንት ስመሠርት ምን እንደ ነበረ፣ገና ወደ ፊት ምን እንደሚሆን፣ይናገር፤ በፊቴ ያስረዳ፤ስለሚመጣውም ነገር አስቀድሞ ይናገር።

8. አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ይህን አልነገርኋችሁምን? ቀድሞስ አላሳወ ቅኋችሁምን?ለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አለን? ፈጽሞ!ወይም ሌላ ዐለት አለ? የለም! ማንንም አላውቅም።”

9. ጣዖት የሚሠሩ ሁሉ ከንቱዎች፣የሚሰሩባቸውም ነገሮች ዋጋ ቢስ ናቸው፤የሚናገሩላቸው ዕውሮች ናቸው፤ዕውቀት የላቸውም ያፍራሉም።

10. ለምንም የማይጠቅመውን አምላክ የሚቀርጽ፣ጣዖትን የሚያበጅስ ማነው?

11. ጣዖት የሚሠራ ሰው እንጂ ሌላ አይደለም፤እርሱና መሰሎቹም ያፍራሉ፤ሁሉም ተሰብስበው በአንድ ላይ ይቁሙ፤ይደነግጣሉ፤ ይዋረዳሉም።

12. ብረት ቀጥቃጭ መሥሪያን ይይዛል፤በከሰል ፍም ላይ ይሠራዋል፤ጣዖትን በመዶሻ ቅርጽ ይሰጠዋል፤በክንዱም ኀይል ያበጀዋል።ከዚያም ይራባል፤ ጒልበት ያጣል፤ውሃ ይጠማል፤ ይደክማል።

13. ጠራቢ በገመድ ይለካል፤በጠመኔ ንድፍ ያወጣል፤በመሮ ይቀርጸዋል፤በጸርከል ምልክት ያደርግበታል።በሰው አምሳል ይቀርጸዋል፤የሰውንም ውበት ያለብሰዋል፤በማምለኪያም ስፍራ ያስቀምጠዋል።

14. ዝግባ ይቈርጣል፤ሾላ ወይም ዋንዛ ይመርጣል፤በደን ውስጥ ካሉት ዛፎች ጋር እንዲያድግ ይተወዋል፤ወይም ጥድን ይተክላል፤ ያንንም ዝናም ያሳድገዋል።

15. ሰው ለማገዶ ይጠቀምበታል፤ከዚያም ጥቂት ወስዶ በማንደድ ይሞቀዋል፤እንጀራም ይጋግርበታል።ከዚሁ ጠርቦ አምላክ ያበጃል፤ያመልከዋል፤ጣዖትን ይሠራል፤ ወድቆም ይሰግድለታል።

16. ግማሹን ዕንጨት ያነደዋል፤በላዩ ምግቡን ያበስልበታል፤ሥጋ ጠብሶበት እስኪጠግብ ይበላል፤እሳቱን እየሞቀ እንዲህ ይላል፤“እሰይ ሞቀኝ፤ እሳቱም ይታየኛል።”

17. በቀረው ዕንጨት የጣዖት አምላኩን ይሠራበታል፤ወድቆ ይሰግድለታል፤ ያመልከዋል፤ወደ እርሱም እየጸለየ፣“አንተ አምላኬ ነህ፤ አድነኝ” ይላል።

18. ምንም አያውቁም፤ አያስተውሉም፤እንዳያዩ ዐይናቸው ተሸፍኖአል፤እንዳያስተውሉ ልባቸው ተዘግቶአል።

19. ማንም ቆም ብሎ አላሰበም፤ዕውቀት ወይም ማስተዋል ስለሌለው እንዲህ ማለት አልቻለም፤“ግማሹን በእሳት አቃጥዬዋለሁ፤በፍሙ እንጀራ ጋግሬበታለሁ፤ሥጋ ጠብሼበት በልቻለሁ፤ታዲያ፣ በቀረው እንዴት ጸያፍ ነገር እሠራለሁ?ለግንድስ መስገድ ይገባኛልን?”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 44