ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 42:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “ደግፌ የያዝሁት አገልጋዬ፣በእርሱም ደስ የሚለኝ ምርጤ ይህ ነው፤መንፈሴን በእርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ለአሕዛብም ፍትሕን ያመጣል።

2. አይጮኽም፣ ቃሉን ከፍ አያደርግም፤ድምፁን በመንገድ ላይ በኀይል አያሰማም።

3. የተቀጠቀጠ ሸምበቆ አይሰብርም፤የሚጤስም የጧፍ ክር አያጠፋም፤ፍትሕን በታማኝነት ያመጣል።

4. ፍትሕን በምድር እስኪያመጣ ድረስ፣አይደክምም፤ ተስፋም አይቈርጥም፤ደሴቶች በሕጉ ይታመናሉ።”

5. ሰማያትን የፈጠረ፣ የዘረጋቸውም፣ምድርንና በውስጧ ያሉትን ሁሉ ያበጀ፣ለሕዝቧ እስትንፋስን፣ለሚኖሩባትም ሕይወትን የሚሰጥ፣ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

6. “እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤እጅህንም እይዛለሁ፤እጠብቅሃለሁ፤ለሕዝቡ ቃል ኪዳን፣ለአሕዛብም ብርሃን አደርግሃለሁ።

7. የዕውሮችን ዐይን ትከፍታለህ፤ምርኮኞችን ከእስር ቤት፣በጨለማ የተቀመጡትንም ከወህኒ ታወጣለህ።

8. “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜም ይህ ነው፤ክብሬን ለሌላ፣ምስጋናዬንም ለጣዖት አልሰጥም።

9. እነሆ፤ የቀድሞው ነገር ተፈጽሞአል፤እኔም አዲስ ነገር እናገራለሁ፤ከመብቀሉም በፊት፣ለእናንተ አስታውቃለሁ።

10. እናንት ወደ ባሕር የምትወርዱ፣ በዚያም ያላችሁ ሁሉ፣ደሴቶችና በዚያ የምትኖሩ በሙሉ፣ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፣ከምድር ዳርቻም ምስጋናውን ዘምሩ።

11. ምድረ በዳውና ከተሞቹ ድምፃቸውን ከፍ ያድርጉ፤ቄዳር ያለችበት መንደር ደስ ይበለው፤የሴላ ሕዝቦች በደስታ ይዘምሩ፤ከተራሮችም ራስ ላይ ይጩኹ።

12. ክብር ለእግዚአብሔር ይስጡ፤ምስጋናውንም በደሴቶች ያውጁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 42