ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 41:15-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. “እነሆ፣ አዲስየተሳለና ብዙ ጥርስ ያለው ማሄጃ አደርግሃለሁ፤ተራሮችን ታሄዳለህ፤ ታደቃቸዋለህ፤ኰረብቶችንም ገለባ ታደርጋቸዋለህ።

16. ታበጥራቸዋለህ፤ ነፋስ ጠርጎ ይወስዳቸዋል፤ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል።አንተ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤በእስራኤል ቅዱስ ሞገስ ታገኛለህ።

17. “ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ዳሩ ግን ምንም አያገኙም፤ጒሮሮአቸው በውሃ ጥም ደርቆአል።ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር እመልስላቸዋለሁ፤እኔ የእስራኤል አምላክ አልተዋቸውም።

18. በተራቈቱ ኰረብቶች ላይ ወንዞችን፣በሸለቆዎች ውስጥ ምንጮች አፈልቃለሁ።ምድረ በዳውን የውሃ ኵሬ፣የተጠማውን ምድር የውሃ ምንጭ አደርጋለሁ።

19. በምድረ በዳ፣ዝግባን፣ ግራርን፣ ባርሰነትንና ወይራን አበቅላለሁ፤በበረሃ፣ ጥድን፣ አስታንናሸውሸዌን በአንድነት እተክላለሁ።

20. ስለዚህ ሰዎች ያያሉ፤ ያውቃሉ፤ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ፣የእስራኤል ቅዱስ እንደ ፈጠረው፣በአንድነት ይገነዘባሉ፤ ያስተውላሉም።

21. “ሙግታችሁን ይዛችሁ ቅረቡ” ይላል እግዚአብሔር፤“ማስረጃችሁን አምጡ” ይላል የያዕቆብ ንጉሥ።

22. “የሚሆነውን እንዲነግሩን፣ጣዖቶቻችሁን አምጡ፤እንድንገነዘብ፣ፍጻሜአቸውን እንድናውቅ፣የቀደሙት ነገሮች ምን እንደ ነበሩ ንገሩን፤ስለሚመጡትም ነገሮች ግለጹልን።

23. እናንት አማልክት መሆናችሁን እናውቅ ዘንድ፣ወደ ፊት ስለሚሆነው ንገሩን፤እንድንደነግጥ፣ በፍርሀት እንድንዋጥ፣መልካምም ሆነ ክፉ፣ አንድ ነገር አድርጉ።

24. እነሆ፤ እናንት ከምንም የማትቈጠሩ ናችሁ፤ሥራችሁ ፈጽሞ ዋጋ ቢስ ነው፤የመረጣችሁም አስጸያፊ ነው።

25. “አንዱን ከሰሜን አስነሣሁት፤ እርሱም ይመጣል፤ከፀሓይ መውጫ የሚመጣው፣ ስሜን የሚጠራ ነው፤ሸክላ ሠሪ ዐፈር እንደሚረግጥ፣አለቆችን እንዲሁ እንደ ጭቃ ይረግጣል።

26. እኛ እናውቅ ዘንድ ይህን ከመጀመሪያው የተናገረ፣‘እርሱ ትክክል ነው’ እንልም ዘንድ ቀድሞ የተናገረ ማነው?ማንም አልተናገረም፤ቀደም ብሎ የተናገረ የለም፤ቃላችሁንም የሰማ የለም።

27. በመጀመሪያ፣ ‘እነሆ፤ ተመልከቺአቸ’ብዬ ለጽዮን የተናገርሁ እኔ ነበርሁ፤ለኢየሩሳሌምምየምሥራች ነጋሪን ሰጥቻለሁ።

28. ተመለከትሁ ማንም አልነበረም፤ከመካከላቸው አማካሪ የለም፤ስጠይቅም መልስ የሚሰጥ የለም።

29. እነሆ፤ ሁሉም ከንቱ ናቸው፤ሥራቸውም መና ነው፤ምስሎቻቸውም ባዶ ነፋስ ናቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 41