ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 41:10-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤አምላክህ ነኝና አትደንግጥ።አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።

11. “እነሆ፤ የተቈጡህ ሁሉ፣እጅግ ያፍራሉ፤ ይዋረዳሉም፤የሚቋቋሙህ፣እንዳልነበሩ ይሆናሉ፤ ይጠፋሉም።

12. ጠላቶችህን ብትፈልጋቸው እንኳ፣አታገኛቸውም፤የሚዋጉህም፣እንዳልነበሩ ይሆናሉ።

13. እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ‘አትፍራ፤እረዳሃለሁ’ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁና።

14. አንት ትል ያዕቆብ፣ታናሽ እስራኤል ሆይ፤‘አትፍራ እኔ እረዳሃለሁ’ ” ይላል እግዚአብሔር፤የሚቤዥህ የእስራኤል ቅዱስ ነው።

15. “እነሆ፣ አዲስየተሳለና ብዙ ጥርስ ያለው ማሄጃ አደርግሃለሁ፤ተራሮችን ታሄዳለህ፤ ታደቃቸዋለህ፤ኰረብቶችንም ገለባ ታደርጋቸዋለህ።

16. ታበጥራቸዋለህ፤ ነፋስ ጠርጎ ይወስዳቸዋል፤ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል።አንተ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤በእስራኤል ቅዱስ ሞገስ ታገኛለህ።

17. “ድኾችና ችግረኞች ውሃ ይፈልጋሉ፤ዳሩ ግን ምንም አያገኙም፤ጒሮሮአቸው በውሃ ጥም ደርቆአል።ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር እመልስላቸዋለሁ፤እኔ የእስራኤል አምላክ አልተዋቸውም።

18. በተራቈቱ ኰረብቶች ላይ ወንዞችን፣በሸለቆዎች ውስጥ ምንጮች አፈልቃለሁ።ምድረ በዳውን የውሃ ኵሬ፣የተጠማውን ምድር የውሃ ምንጭ አደርጋለሁ።

19. በምድረ በዳ፣ዝግባን፣ ግራርን፣ ባርሰነትንና ወይራን አበቅላለሁ፤በበረሃ፣ ጥድን፣ አስታንናሸውሸዌን በአንድነት እተክላለሁ።

20. ስለዚህ ሰዎች ያያሉ፤ ያውቃሉ፤ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ፣የእስራኤል ቅዱስ እንደ ፈጠረው፣በአንድነት ይገነዘባሉ፤ ያስተውላሉም።

21. “ሙግታችሁን ይዛችሁ ቅረቡ” ይላል እግዚአብሔር፤“ማስረጃችሁን አምጡ” ይላል የያዕቆብ ንጉሥ።

22. “የሚሆነውን እንዲነግሩን፣ጣዖቶቻችሁን አምጡ፤እንድንገነዘብ፣ፍጻሜአቸውን እንድናውቅ፣የቀደሙት ነገሮች ምን እንደ ነበሩ ንገሩን፤ስለሚመጡትም ነገሮች ግለጹልን።

23. እናንት አማልክት መሆናችሁን እናውቅ ዘንድ፣ወደ ፊት ስለሚሆነው ንገሩን፤እንድንደነግጥ፣ በፍርሀት እንድንዋጥ፣መልካምም ሆነ ክፉ፣ አንድ ነገር አድርጉ።

24. እነሆ፤ እናንት ከምንም የማትቈጠሩ ናችሁ፤ሥራችሁ ፈጽሞ ዋጋ ቢስ ነው፤የመረጣችሁም አስጸያፊ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 41