ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 14:10-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. እነርሱ ሁሉ ይመልሱልሃል፤እንዲህም ይሉሃል፤“አንተም እንደ እኛ ደከምህ፤እንደ እኛም ሆንህ።”

11. ክብርህ፣ ከነበገና ድምፁወደ ሲኦል ወረደ፤ብሎች ከበታችህ ተነጥፈዋል፤ትሎችም መደረቢያህ ይሆናሉ።

12. አንተ የንጋት ልጅ፣ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፤እንዴት ከሰማይ ወደቅአንተ ቀድሞ መንግሥታትን ያዋረድህ፤እንዴት ወደ ምድር ተጣልህ!

13. በልብህም እንዲህ አልህ፤“ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፤ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ አደርጋለሁ፤በተራራው መሰብሰቢያ፣በተቀደሰውም ተራራ ከፍታ ላይ በዙፋኔእቀመጣለሁ፤

14. ከደመናዎችም ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፤ራሴንም እንደ ልዑል አደርጋለሁ።”

15. ነገር ግን ወደ ሲኦል፣ወደ ጥልቁም ጒድጓድ ወርደሃል።

16. የሚያዩህም አትኵረው እየተመለክቱህ፣በመገረም ስለ አንተ እንዲህ ይላሉ፤“ያ ምድርን ያናወጠ፣መንግሥታትን ያንቀጠቀጠ፣ ይህ ሰው ነውን?

17. ዓለምን ምድረ በዳ ያደረገ፤ከተሞችን ያፈራረሰ፣ምርኮኞቹንም ወደ አገራቸው እንዳይሄዱ የከለከለ ይህ ነውን?”

18. የአሕዛብ ነገሥታት ሁሉ በክብር አንቀላፍተዋል፤በየመቃብራቸው ዐርፈዋል።

19. አንተ ግን እንደማይፈለግ ቅርንጫፍ፣ከመቃብር ወጥተህ ተጥለሃል፤በሰይፍ በተወጉት፣ወደ ጥልቁ ድንጋዮች በወረዱት፣በተገደሉትም ተሸፍነሃል።እንደ ተረገጠም ሬሳ ሆነሃል።

20. ከእነርሱ ጋር በመቃብር አትሆንም፤ምድርህን አጥፍተሃልና፤ሕዝብህንም ፈጅተሃልና።የክፉ አድራጊዎች ዘርፈጽሞ አይታወስም።

21. ተነሥተው ምድርን እንዳይወርሱ፣ዓለምንም በከተሞቻቸው እንዳይሞሉ፣ስለ አባቶቻቸው ኀጢአት፣ወንድ ልጆቹ የሚታረዱበትን ስፍራ አዘጋጁ።

22. “በእነርሱ ላይ እነሣለሁ”ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።“ስሟንና ትሩፋኖቿን፣ዘሯንና ትውልዷን ከባቢሎን እቈርጣለሁ”ይላል እግዚአብሔር።

23. “የጃርት መኖሪያ፣ረግረጋማ ቦታ አደርጋታለሁ፤በጥፋትም መጥረጊያ እጠርጋታለሁ”ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

24. የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል፤“እንደ ዐቀድሁት በርግጥ ይከናወናል፤እንደ አሰብሁትም ይሆናል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 14