ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አስቴር 9:20-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. መርዶክዮስ የተፈጸሙትን እነዚህን ድርጊቶች ጻፈ፤ ደብዳቤ አዘጋጅቶም በመላው የንጉሥ ጠረክሲስ አውራጃ በቅርብና በሩቅ ለሚገኙት አይሁድ ሁሉ ላከ፤

21. የላከውም የአዳርን ወር ዐሥራ አራተኛና ዐሥራ አምስተኛ ቀን በየዐመቱ እንዲያከብሩ ነው፤

22. የሚያከብሩበትም ምክንያት አይሁድ ከጠላቶቻቸው ዕረፍት ያገኙበት፣ ሐዘናቸው ወደ ደስታ፣ ልቅሷቸውም ወደ ክብረ በዓል የተለወጠበት ቀን ስለ ሆነ ነው። ቀኖቹንም የተድላና የደስታ ቀኖች አድርገው፣ እርስ በርሳቸውም የምግብ ስጦታ እየተለዋወጡና ለድኾችም ስጦታ እየሰጡ እንዲያከብሩ ጻፈላቸው።

23. ስለዚህ አይሁድ መርዶክዮስ የጻፈላቸውን ለመፈጸምና የጀመሩትን በዓል ለማክበር ተስማሙ፤

24. ምክንያቱም የአይሁድ ሁሉ ጠላት የሆነው የአጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ አይሁድን ለማጥፋት አሢሮ ነበር፤ ሊፈጃቸውና ሊያጠፋቸውም ፉር የተባለ ዕጣ ጥሎ ነበር።

25. ሤራው በንጉሡ ዘንድ እንደ ታወቀ ሐማ በአይሁድ ላይ የሸረበው ሤራ በገዛ ራሱ ላይ እንዲጠመጠም፣ እርሱና ወንዶች ልጆቹም በዕንጨት ላይ እንዲሰቀሉ የጽሑፍ ትእዛዝ አስተላለፈ።

26. ስለዚህ እነዚህ ቀኖች ፉር ከሚለው ቃል “ፉሪም” ለመባል በቁ። በዚህ ደብዳቤ ስለ ተጻፈው ሁሉ፣ ስላዩትና ስለ ደረሰባቸውም ነገር ሁሉ፣

27. አይሁድ በታዘዘውና በተወሰነው ጊዜ እነርሱና ዘሮቻቸው፣ እነርሱን የተጠጓቸውም ሁሉ እነዚህን ሁለት ቀኖች በየዓመቱ ባለማቋረጥ እንዲያከብሩ ሥርዐት አድርገው ራሳቸው ወሰኑ።

28. እነዚህም ቀኖች በእያንዳንዱ ትውልድ፣ በእያንዳንዱ ቤተ ሰብ፣ በእያንዳንዱ አውራጃና በእያንዳንዱ ከተማ መታሰብና መከበር ይኖርባቸዋል፤ ይኸውም እነዚህ የፉሪም ቀኖች በአይሁድ ዘንድ ሳይከበሩ እንዳይቀሩ፤ መታሰቢያቸውም ከዘሮቻቸው መካከል እንዳይደመሰስ ነው።

29. ስለዚህ የአቢካኢል ልጅ ንግሥት አስቴር ከአይሁዳዊው ከመርዶክዮስ ጋር በመሆን፣ ፉሪምን አስመልክተው ይህችን ሁለተኛዪቱን ደብዳቤ ለማጽናት በሙሉ ሥልጣን ጻፉ።

30. መርዶክዮስም የመልካም ምኞት መግለጫና ማረጋገጫ የሆነውን ደብዳቤ በጠረክሲስ ግዛት ውስጥ በሚገኙት አንድ መቶ ሃያ ሰባት አውራጃዎች ለሚኖሩት አይሁድ ሁሉ ላከ፤

31. የላከውም አይሁዳዊው መርዶክዮስና ንግሥት አስቴር ባወጁላቸውና እንደዚሁም የጾሙንና የሰቈቃውን ጊዜ በሚመለከት ለራሳቸውና ለዘራቸው ባጸኑት ውሳኔ መሠረት እነዚህ የፉሪም ቀኖች በተወሰነላቸው ጊዜ እንዲከበሩ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አስቴር 9