ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 9:13-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. “በሲና ተራራ ላይ ወረድህ፤ ከሰማይም ተናገርሃቸው። ትክክለኛ ደንቦችንና እውነተኛ ሕጎችን፣ መልካም ሥርዐቶችንና ትእዛዞችን ሰጠሃቸው።

14. የተቀደሰች ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፤ ትእዛዞችን፣ ሥርዐቶችንና ሕጎችን በባሪያህ በሙሴ አማካይነት ሰጠሃቸው።

15. በተራቡ ጊዜ ከሰማይ መና ሰጠሃቸው፤ በተጠሙም ጊዜ ከዐለት ውሃ አፈለቅህላቸው፤ ልትሰጣቸው በተዘረጋች እጅ ወደ ማልህላቸውም ምድር ገብተው እንዲወርሱ አዘዝሃቸው።

16. “እነርሱና አባቶቻችን ግን ትምክሕ ተኞችና ዐንገተ ደንዳኖች ሆኑ፤ ትእዛዞችህንም አልፈጸሙም።

17. ለመስማት አልፈለጉም፤ በመካከላቸውም ያደረግሃቸውን ታምራት ማስታወስ አልቻሉም። ዐንገታቸውን አደነደኑ፤ በዐመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ለመመለስ መሪ ሾሙ። አንተ ግን ይቅር ባይ አምላክ፣ ቸርና ርኅሩኅ፣ ለቍጣም የዘገየህና ምሕረትህ የበዛ ነህ። ስለዚህ አልተውሃቸውም፤

18. የጥጃ ምስል ለራሳቸው አቅልጠው፣ ‘ከግብፅ ያወጣህ አምላክ ይህ ነው’ ባሉና አስጸያፊ የስድብ ቃል በተናገሩ ጊዜ እንኳ አልተለየሃቸውም።

19. “ከርኅራኄህ ብዛት የተነሣ በምድረ በዳ አልተውሃቸውም፤ ቀን የደመናው ዐምድ በመንገዳቸው ላይ መምራቱን፣ ሌሊትም የእሳቱ ዐምድ በሚሄዱበት ላይ ማብራቱን አላቆመም።

20. ያስተምራቸው ዘንድ ቸር መንፈስህን ሰጠሃቸው፤ መናውን ከአፋቸው አልከለከልህም፤ በተጠሙ ጊዜ ውሃ ሰጠሃቸው።

21. በምድረ በዳ አርባ ዓመት መገብሃቸው፤ ምንም ያጡት አልነበረም፤ ልብሳቸው አላለቀም፤ እግራቸውም አላበጠም።

22. “በሩቅ የሚገኙትን ድንበሮች እንኳ ሳይቀር፣ መንግሥታትንና አሕዛብን ሰጠሃቸው። የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፣ የባሳን ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ።

23. ወንዶች ልጆቻቸውን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛሃቸው፤ አባቶቻቸው ገብተው እንዲወርሱ ወዳዘዝሃቸውም ምድር አገባሃቸው።

24. በምድሪቱ ወንዶች ልጆቻቸው ገቡባት፤ ወረሷትም። በምድሪቱ ላይ ይኖሩ የነበሩትን ከነዓናውያን በፊታቸው አንበረከክህ፤ ያሻቸውን ያደርጉባቸው ዘንድ ከነዓናውያንን ከንጉሦቻቸውና ከምድሪቱ ሕዝቦች ጋር በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው።

25. የተመሸጉ ከተሞቻቸውንና የሰባውን ምድር ያዙ፤ በመልካም ነገር ሁሉ የተሞሉ ቤቶቻቸውን፣ የተቈፈሩ የውሃ ጒድጓዶቻቸውን፣ የወይን ተክላቸውን፣ የወይራ ዛፎቻቸውንና ስፍር ቍጥር የሌላቸውን የፍሬ ዛፎች ያዙ። እስኪጠግቡ በሉ፤ ወፈሩም፤ በታላቅ በጎነትህም ደስ ተሰኙ።

26. “ነገር ግን እንቢተኞች ሆኑ፤ ዐመፁብህም፤ ሕግህንም አሽቀንጥረው ጣሉ፤ ወደ አንተ እንዲመለሱ ሲያስጠነቅቋቸው የነበሩት ነቢያትህን ገደሉ፤ አስጸያፊ የስድብ ቃልም ተናገሩ።

27. ስለዚህ ላስጨነቋቸው ጠላቶቻቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። በተጨነቁ ጊዜ ግን ወደ አንተ ጮኹ፤ አንተም ከሰማይ ሰማሃቸው፤ ከርኅራኄህም ብዛት የተነሣ ከጠላቶቻቸው እጅ የሚያድኗቸውን ታዳጊዎች ሰጠሃቸው።

28. “ነገር ግን ዕረፍት ባገኙ ጊዜ፣ በፊትህ ክፉውን ነገር እንደ ገና ፈጸሙ፤ ከዚያም ይገዟቸው ዘንድ በጠላቶቻቸው እጅ ጣልሃቸው፤ እንደ ገና ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ፣ ከሰማይ ሰማህ፤ በርኅራኄህም በየጊዜው ታደግሃቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ነህምያ 9