ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሕዝቡ ሁሉ “ከውሃ በር” ፊት ለፊት በሚገኘው አደባባይ ላይ እንደ አንድ ሰው ተሰበሰቡ፤ ከዚያም እግዚአብሔር ለእስራኤል ያዘዘውን የሙሴ ሕግ መጽሐፍ እንዲያመጣ ለጸሓፊው ለዕዝራ ነገሩት።

2. ስለዚህ ካህኑ ዕዝራ በሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ወንዶች፣ ሴቶችና ማስተዋል የሚችሉ ሁሉ በተገኙበት ጉባኤ ፊት የሕጉን መጽሐፍ አመጣ።

3. እርሱም “በውሃ በር” ትይዩ ወደሚገኘው አደባባይ ፊቱን አቅንቶ፣ በወንዶች፣ በሴቶችና በሚያስተውሉ ሰዎች ሁሉ ፊት በመቆም፣ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ቀትር ድረስ ድምፁን ከፍ አድርጎ አነበበ፤ ሕዝቡም ሁሉ የሕጉን መጽሐፍ በጥሞና አደመጡ።

4. ጸሓፊው ዕዝራ ለዚሁ ተብሎ በተሠራውና ከፍ ብሎ በሚገኘው የዕንጨት መድረክ ላይ ቆሞ ነበር፤ በአጠገቡም በስተ ቀኙ በኩል መቲትያ፣ ሽማዕ፣ ዓናያ፣ ኦርዮ፣ ኬልቅያስ፣ መዕሤያ፣ በስተ ግራው በኩል ደግሞ ፈዳያ፣ ሚሳኤል፣ መልክያ፣ ሐሱም፣ ሐሸበዳ፣ ዘካርያስና ሜሱላም ቆመው ነበር።

5. ዕዝራም መጽሐፉን ከፈተ፤ ከሕዝቡ ከፍ ብሎ ቆሞ ስለ ነበረ፣ ሁሉም ያዩት ነበረ፣ በከፈተውም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቆሙ።

6. ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ሕዝቡም ሁሉ እጆቻቸውን በማንሣት፣ “አሜን! አሜን!” ብለው መለሱ፤ ከዚህ በኋላ በግምባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ።

7. ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ባኒ፣ ሰራብያ፣ ያሚን፣ ዓቁብ፣ ሳባታይ፣ ሆዲያ፣ መዕሤያ፣ ቆሊጣስ፣ ዓዛርያስ፣ ዮዛባት፣ ሐናን፣ ፌልያ ሕዝቡ በዚያው ቆመው እንዳሉ ሕጉን አስረዷቸው።

8. ሕዝቡ የሚነበበውን መረዳት እንዲችሉ ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ካነበቡላቸው በኋላ ይተረጒሙላቸውና ይተነትኑላቸው ነበር።

9. ከዚያም አገረ ገዡ ነህምያ፣ ካህኑና ጸሓፊው ዕዝራ፣ ሕዝቡንም የሚያስተምሩት ሌዋውያን፣ “ይህች ቀን ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የተቀደሰች ናት፤ አትዘኑ፤ አታልቅሱም” አሏቸው፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ሁሉ የሕጉን ቃል በሚሰሙበት ጊዜ ያለቅሱ ነበር።

10. ነህምያም፣ “ሂዱ፤ ጥሩ ምግብ በመብላት፣ ጣፋጩን በመጠጣት ደስ ይበላችሁ፤ ምንም የተዘጋጀ ነገር ለሌላቸውም ካላችሁ ላይ ከፍላችሁ ላኩላቸው። ይህች ቀን ለጌታችን የተቀደሰች ናት፤ የእግዚአብሔር ደስታ ብርታታችሁ ስለ ሆነ አትዘኑ” አላቸው።

11. ሌዋውያኑም፣ “ይህች ቀን የተቀደሰች ስለሆነች ዝም በሉ፤ አትዘኑም” በማለት ሕዝቡን ሁሉ አረጋጉ።

12. ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ የተነገራቸውን ቃል ተረድተው ስለ ነበረ፣ ለመብላት፣ ለመጠጣት፣ ከምግባቸው ከፍለው ለመላክና ሐሤትም ለማድረግ ሄዱ።

13. ከወሩም በሁለተኛው ቀን የየቤተ ሰቡ ሁሉ ኀላፊዎች፣ የሕጉን ቃል ለመማር ከካህናቱና ከሌዋውያኑ ጋር በጸሓፊው በዕዝራ ዙሪያ ተሰበሰቡ።

14. እስራኤላውያን በሰባተኛው ወር በሚውለው በዓል በዳስ ውስጥ እንዲቀመጡ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት የሰጠውን ትእዛዝ በሕጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ፤

15. ስለዚህ በየከተሞቻቸውና በኢየሩሳሌም ይህን ቃል እንዲያውጁና እንዲያሠራጩ እንዲህ በማለት አዘዟቸው፤ “ወደ ኰረብቶች ውጡ፤ ከዘይትና ከበረሓ ወይራ፣ ከባርስነት፣ ከዘንባባና ከለምለም ዛፎች ቅርንጫፎችን አምጡ፤ በተጻፈው መሠረት ዳሶችን ሥሩ።”

16. ስለዚህ ሕዝቡ ወጥተው ቅርንጫፎች አመጡ፤ እያንዳንዳቸውም በየቤታቸው ጣራ ሰገነት፣ በየግቢያቸው፣ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ፣ “በውሃ በር” አደባባይና በኤፍሬም በር አደባባይ ላይ ዳስ ሠሩ።

17. ከምርኮ የተመለሰውም ማኅበር ሁሉ ዳሱን ሠርቶ ተቀመጠ። ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያን ጊዜ ድረስ እስራኤላውያን እንደዚያ አድርገው በዓሉን አክብረው አያውቁም፤ ደስታቸውም ታላቅ ነበር።

18. ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ፣ ዕዝራ በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ያነብ ነበር። እነርሱም በዓሉን ሰባት ቀን አከበሩ፤ በስምንተኛውም ቀን በሕጉ መሠረት የተቀደሰ ጉባኤ ተደረገ።