ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ነህምያ 13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ነህምያ በመጨረሻ የወሰደው የተሐድሶ እርምጃ

1. በዚያም ቀን የሙሴን መጽሐፍ ከፍ ባለ ድምፅ ለሕዝቡ አነበቡ፤ አሞናዊም ሆነ ሞዓባዊ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ፈጽሞ እንዳይገባ የሚከለክል ተጽፎ ተገኘ፤

2. ይህ የሆነው እስራኤልን በምግብና ውሃ መስተንግዶ በመቀበል ፈንታ፣ በለዓም እንዲረግምላቸው በገንዘብ ስለ ገዙት ነበር። ይሁን እንጂ አምላካችን ርግማኑን ወደ በረከት ለወጠው።

3. ሕዝቡም ይህን ሕግ በሰሙ ጊዜ፣ የባዕድ ወገን የሆኑትን ሁሉ ከእስራኤል ለዩ።

4. ቀድሞ የአምላካችን ዕቃ ቤቶች ኀላፊ ሆኖ የተሾመው ካህኑ ኤልያሴብ ነበር፤ እርሱም ከጦብያ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነበረው፤

5. ከዚህ በፊት የእህል ቍርባኑ፣ ዕጣኑ፣ የቤተ መቅደሱ ዕቃዎች፣ የእህሉ ዐሥራትና፣ ለሌዋውያን፣ ለመዘምራንና ለበር ጠባቂዎች የታዘዘው አዲሱ ወይንና ዘይት፣ ለካህናቱም የሚመጣው ስጦታ ይቀመጥበት የነበረውን ትልቁን የዕቃ ቤት እንዲኖርበት ሰጥቶት ነበር።

6. ይህ ሁሉ ሲሆን እኔ በኢየሩሳሌም አልነበርሁም፤ ምክንያቱም በባቢሎን ንጉሥ በአርጤክስስ ሠላሳ ሁለተኛ ዓመት ተመልሼ ወደ ንጉሡ ሄጄ ነበር። ከጥቂት ጊዜም በኋላ የንጉሡን ፈቃድ ጠይቄ

7. ወደ ኢየሩሳሌም ተመለስሁ፤ በዚያም ኤልያሴብ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ለጦብያ አንድ መኖሪያ ክፍል በመስጠት የፈጸመውን ክፉ ድርጊት ተረዳሁ።

8. እኔም በጣም ዐዘንሁ፤ የጦብያንም የቤት ዕቃ ሁሉ ከክፍሉ እያወጣሁ ወደ ውጭ ጣልሁ።

9. ክፍሎቹንም እንዲያነጹ ትእዛዝ ሰጠሁ፤ ከዚያም የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች፣ የእህሉን ቍርባንና ዕጣኑን ጭምር መልሼ አስገባሁ።

10. እንዲሁም ለሌዋውያን የተመደበው ድርሻ እንዳልተሰጣቸውና አገልግሎቱን በኀላፊነት የሚመሩ ሌዋውያንና መዘምራን ሁሉ ወደየርስታቸው መመለሳቸውን ተረዳሁ።

11. ስለዚህ ሹማምቱን ገሥጬ፣ “ቤተ መቅደሱ እስከዚህ ቸል የተባለው ለምንድን ነው?” ብዬ ጠየቅኋቸው። ከዚያም እነርሱን በአንድነት ሰብስቤ ወደ ምድብ ሥራቸው እንዲመለሱ አደረግሁ።

12. ይሁዳም ሁሉ የእህሉን፣ የአዲሱን ወይንና የዘይቱን ዐሥራት ወደ ዕቃ ቤቶቹ አስገቡ።

13. ለዕቃ ቤቶቹም ካህኑን ሰሌምያን፣ ጸሓፊውን ሳዶቅንና ፈዳያ የተባለውን ሌዋዊ ኀላፊ አድርጌ ሾምሁ፤ መደብሁ፤ እንዲሁም የመታንያን ልጅ፣ የዘኩርን ልጅ ሐናን ረዳታቸው አደረግሁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ታማኞች ነበሩ። ሥራቸውም ለወንድሞቻቸው የተመደበውን ቀለብ ማከፋፈል ነበረ።

14. አምላኬ ሆይ፤ ስለዚህ ነገር አስበኝ፤ ለአምላኬ ቤትና ለአገልግሎቱ ስል በታማኝነት ያከናወንሁትን አታጥፋ።

15. በእነዚያ ቀናት በይሁዳ በሰንበት ቀን የወይን መጭመቂያ የሚረግጡ፣ እህል የሚያስገቡና፣ የወይን ጠጅ፣ የወይን ዘለላ፣ የበለስና ሌሎችን የጭነት ዐይነቶች ሁሉ በአህያ ላይ የሚጭኑ ሰዎች አየሁ፤ ይህን ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ያስገቡ የነበረው በሰንበት ቀን ነበረ። ስለዚህ በዚያን ቀን ምግብ እንዳይሸጡ ከለከልኋቸው።

16. በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የጢሮስ ሰዎችም ዓሣና ልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጥ በሰንበት ቀን እያመጡ ለይሁዳ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ይሸጡ ነበር።

17. እኔም የይሁዳን መኳንንት በመገሠጽ እንዲህ አልኋቸው፤ “ሰንበትን በማርከስ ይህ የምትፈጽሙት ክፉ ድርጊት ምንድን ነው?

18. የቀድሞ አባቶቻችሁ ያደረጉት ይህንኑ አልነበረምን? አምላካችንስ ይህን ሁሉ ጥፋት በእኛና በዚች ከተማ ላይ ያመጣው በዚሁ በደላችን አይደለምን? አሁንም እናንተ ሰንበትን በማርከስ የባሰ መከራ በእስራኤል ላይ ታመጣላችሁ።”

19. በሰንበት ዋዜማ በኢየሩሳሌም በሮች ላይ የምሽቱ ጥላ ማረፍ ሲጀምር በሮቹ እንዲዘጉና፣ ሰንበት እስኪያልፍ ድረስ እንዳይከፈቱ አዘዝሁ፤ በሰንበት ቀን ጭነት እንዳይገባም ከራሴ ሰዎች አንዳንዶቹን በየበሩ ላይ አቆምሁ።

20. የልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴዎችና ቸርቻሪዎች ከኢየሩሳሌም ውጭ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ አድረዋል።

21. እኔ ግን፣ “ከቅጥሩ ውጭ የምታድሩት ለምንድን ነው? እንዲህ ያለውን ነገር ዳግመኛ ብታደርጉ እጄን አነሣባችኋለሁ” ስል አስጠነቀቅኋቸው፤ እነርሱም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሰንበት ቀን አልመጡም።

22. ከዚያም ሌዋውያኑ ራሳቸውን እንዲያነጹ፣ ሄደውም የቅጥሩን በር እንዲጠብቁና የሰንበትንም ቀን እንዲቀድሱ አዘዝኋቸው።አምላኬ ሆይ፤ ስለዚህም ደግሞ አስበኝ፤ እንደ ታላቅ ፍቅርህም ብዛት ምሕረት አድርግልኝ።

23. በእነዚያም ቀናት የአሽዶድን፣ የአሞንንና የሞዓብን ሴቶች ያገቡ አይሁድ አገኘሁ።

24. ከልጆቻቸውም እኩሌቶቹ የአሽዶድን፣ ወይም ከሌሎቹ ሕዝቦች የአንዱን ቋንቋ እንጂ የአይሁድን ቋንቋ መናገር አይችሉም ነበር።

25. እኔም ገሠጽኋቸው፤ ርግማንም አወረድሁባቸው። አንዳንዶቹን መታኋቸው፤ ጠጒራቸውንም ነጨሁ። በእግዚአብሔር ስም እንዲህ ስል አማልኋቸው፤ “ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ።

26. የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ኀጢአት የሠራው እንዲህ ከመሰለው ጋብቻ የተነሣ አይደለምን? በብዙ መንግሥታት መካከል እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ አልነበረም፤ በአምላኩም የተወደደ ነበረ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ሁሉ ላይ ንጉሥ አደረገው። ነገር ግን ባዕዳን ሴቶች ወደ ኀጢአት መሩት።

27. እናንተም ደግሞ ባዕዳን ሴቶችን በማግባት ይህን የመሰለ ታላቅ በደል እንደምትፈጽሙና ለአምላካችንም ታማኞች እንዳልሆናችሁ መስማት ይገባናልን?

28. ከሊቀ ካህኑ ከኤልያሴብ ልጅ ከዮአዳ ልጆች አንዱ የሖሮናዊው የሰንባላጥ አማች ነበረ፤ እኔም ከአጠገቤ አባረርሁት።

29. አምላኬ ሆይ፤ የክህነትን ማዕረግ፣ የክህነትንና የሌዋውያንን ቃል ኪዳን ስላረከሱ አስባቸው።

30. ስለዚህ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ከማናቸውም ባዕድ ነገር ሁሉ አነጻኋቸው፤ የእያንዳንዱንም ተግባር በመለየት በየሥራ ቦታቸው መደብኋቸው።

31. በተወሰነው ጊዜ ስለሚዋጣውም የማገዶ ዕንጨትና ስለ በኵራቱ መመሪያ ሰጠሁ።አምላኬ ሆይ፤ በቸርነት አስበኝ።