ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሚክያስ 3:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም እኔ እንዲህ አልሁ፤“እናንት የያዕቆብ መሪዎች፤እናንት የእስራኤል ቤት ገዦች ስሙ፤ፍትሕን ማወቅ አይገባችሁምን?

2. መልካሙን ጠላችሁ፤ ክፉውንም ወደዳችሁ፤የሕዝቤን ቈዳ ገፈፋችሁ፤ሥጋቸውንም ከዐጥንቶቻቸው ለያችሁ፤

3. የሕዝቤን ሥጋ በላችሁ፤ቈዳቸውን ገፈፋችሁ፤ዐጥንቶቻቸውንም ሰባበራችሁ፤በመጥበሻ እንደሚጠበስ፣በድስት እንደሚቀቀል ሥጋ ቈራረጣችኋቸው።

4. እነርሱም ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ፤እርሱ ግን አይመልስላቸውም፤ካደረጉት ክፋት የተነሣ፣በዚያ ጊዜ ፊቱን ከእነርሱ ይሰውራል።

5. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ሕዝቤን የሚያስቱ ነቢያት፣ሰው ሲያበላቸው፣ ‘ሰላም አለ’ ይላሉ፤ሳያበላቸው ሲቀር ግን፣ጦርነት ሊያውጁበት ይነሣሉ።

6. ስለዚህ ሌሊቱ ያለ ራእይ፣ጨለማውም ያለ ንግርት ይመጣባችኋል፤በነቢያት ላይ ፀሐይ ትጠልቅባቸዋለች፤ቀኑም ይጨልምባቸዋል።

7. ባለ ራእዮች ያፍራሉ፤ንግርተኞችም ይዋረዳሉ፤ሁሉም ፊታቸውን ይሸፍናሉ፤ከእግዚአብሔር መልስ የለምና።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሚክያስ 3