ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መክብብ 9:3-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ከፀሓይ በታች በሁሉም ላይ የሚሆነው ክፋት ይህ ነው፤ የሁሉም የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ አንድ ነው። በዚህም ላይ የሰዎች ልብ በክፋት የተሞላ ነው፤ በሕይወት እያሉም በልባቸው ውስጥ እብደት አለ፤ በመጨረሻም ወደ ሙታን ይወርዳሉ።

4. በሕያዋን መካከል ያለ ማንኛውም ሰው ተስፋ አለው፤ በሕይወት ያለ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና!

5. ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ሙታን ግን ምንም አያውቁምና፤መታሰቢያቸው ይረሳል፤ምንም ዋጋ የላቸውም።

6. ፍቅራቸው፣ ጥላቻቸው፣ቅናታቸውም ከጠፋ ቈይቶአል፤ከፀሓይ በታች በሚሆነው ነገር ሁሉ፣ፈጽሞ ዕጣ ፈንታ አይኖራቸውም።

7. ሂድ፤ ምግብህን በደስታ ብላ፤ ወይንህንም ልብህ ደስ ብሎት ጠጣ፤ ባደረግኸው ነገር እግዚአብሔር ደስ ብሎታልና።

8. ዘወትር ልብስህ ነጭ ይሁን፤ ራስህንም ዘወትር በዘይት ቅባ።

9. እግዚአብሔር ከፀሓይ በታች በሰጠህ በዚህ ትርጒም የለሽ የሕይወት ዘመን ሁሉ፣ ከንቱ በሆኑትም ቀኖችህ ሁሉ ከምትወዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ፤ በሕይወትህና ከፀሓይ በታች በምትደክምበት ነገር ሁሉ ይህ ዕድል ፈንታህ ነውና።

10. እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኀይልህ ሥራው፤ ልትሄድበት ባለው መቃብር ውስጥ መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለምና።

11. ሌላም ነገር ከፀሓይ በታች አየሁ፡ሩጫ ለፈጣኖች፣ውጊያም ለኀያላን አይደለም፤እንጀራ ለጥበበኞች፣ወይም ባለጠግነት ለብልሆች፣ወይም ሞገስ ለዐዋቂዎች አይሆንም፤ጊዜና ዕድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል።

12. ደግሞም የራሱን ጊዜ የሚያውቅ ሰው የለም፤ዓሦች በክፉ መረብ እንደሚያዙ፣ወይም ወፎች በወጥመድ እንደሚጠመዱ፣ሰዎችም ሳያስቡት በሚመጣባቸው፣በክፉ ጊዜ ይጠመዳሉ።

13. እንዲሁም እጅግ ያስገረመኝን ይህን የጥበብ ምሳሌ ከፀሓይ በታች አየሁ፦

14. ጥቂት ሰዎች የሚኖሩባት አንዲት ትንሽ ከተማ ነበረች፤ አንድ ኀያል ንጉሥም መጣባት፤ ከበባት፤ በላይዋም ትልቅ ምሽግ ሠራባት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መክብብ 9