ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መክብብ 2:8-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ለራሴም ብርንና ወርቅን፣ የነገሥታትና የአውራጃዎችን ሀብት አካበትሁ፤ ወንድና ሴት አዝማሪዎች፣ የሰው መደሰቻ የሆኑ ቅምጦች ነበሩኝ።

9. ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ እጅግ ታላቅ ሆንሁ፤ በዚህ ሁሉ ጥበቤ ከእኔ ጋር ነበረች።

10. ዐይኔ የፈለገውን ሁሉ አልከለከልሁትም፤ለልቤም ምድራዊ ደስታን አልነፈግሁትም፤ልቤ በሠራሁት ሁሉ ደስ አለው፤ይህም የድካሜ ሁሉ ዋጋ ነበረ።

11. ሆኖም እጆቼ የሠሩትን ሁሉ፣ለማግኘትም የደከምሁትን ድካም ሁሉ ሳስብ፣ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፤ከፀሓይ በታች ምንም ትርፍ አልነበረም።

12. ከዚያም ጥበብን፣እብደትንና ሞኝነትን ለመመርመር ሐሳቤን መለስሁ፤አስቀድሞ ከተደረገው በቀር፣ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ሊያደርግ ይችላል?

13. ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ ሁሉ፣ጥበብም ከሞኝነት እንደሚበልጥ ተመለከትሁ።

14. የጠቢብ ሰው ዐይኖች ያሉት በራሱ ውስጥ ነው፤ሞኝ ግን በጨለማ ውስጥ ይራመዳል፤ሆኖም የሁለቱም ዕድል ፈንታ፣አንድ መሆኑን ተገነዘብሁ።

15. ከዚያም በልቤ፣“የሞኙ ዕድል ፈንታ በእኔም ላይ ይደርሳል፤ታዲያ ጠቢብ በመሆኔ ትርፌ ምንድን ነው?” አልሁ።በልቤም፣“ይህም ደግሞ ከንቱ ነው” አልሁ።

16. ጠቢቡም ሰው እንደ ሞኙ ለዘላለም አይታወስምና፤በሚመጡት ዘመናት ሁለቱም ይረሳሉ።ለካ፣ ጠቢቡምእንደ ሞኙ መሞቱ አይቀርም!

17. ስለዚህ ከፀሓይ በታች የሚሠራው ሥራ አሳዛኝ ስለ ሆነብኝ ሕይወትን ጠላሁ፤ ይህም ሁሉ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።

18. ከፀሓይ በታች የደከምሁበትን ነገር ሁሉ ጠላሁት፣ ከኋላዬ ለሚመጣው የግድ እተውለታለሁና።

19. እርሱ ጠቢብ ወይም ሞኝ ይሆን እንደሆነ ማን ያውቃል? ሆኖም ከፀሓይ በታች ድካሜንና ችሎታዬን ባፈሰ ስሁበት ሥራ ሁሉ ላይ ባለቤት ይሆንበታል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።

20. ስለዚህ ከፀሓይ በታች በደከምሁበት ነገር ሁሉ ላይ ልቤ ተስፋ መቊረጥ ጀመረ፤

21. ምክንያቱም ሰው ሥራውን በጥበብ፣ በዕውቀትና በብልኀት ሠርቶ፣ ከዚያ ያለውን ሁሉ ለሌላ ላልለፋበት ሰው ይተውለታል። ይህም ደግሞ ከንቱና ትልቅ ጒዳት ነው።

22. ሰው ከፀሓይ በታች በሚደክምበት ጥረትና ልፋት ሁሉ ትርፉ ምንድን ነው?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መክብብ 2