ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 7:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ይሩበኣል የተባለው ጌዴዎን፣ ከእርሱም ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ በጠዋት ተነሥተው በሐሮድ ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ። የምድያማውያንም ሰፈር እስራኤላውያን ከሰፈሩበት በስተ ሰሜን በኩል፣ በሞሬ ኰረብታ አጠገብ በሸለቆው ውስጥ ነበር።

2. እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ምድያማውያንን በእጃቸው አሳልፌ እንዳ ልሰጥ አብረውህ ያሉት ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው፤ እስራኤላውያን የገዛ ኀይላቸው እንዳዳናቸው በመቍጠር እንዳይታበዩብኝ፣

3. ‘ማንም የፈራ ቢኖር የገለዓድን ተራራ ትቶ ወደ መጣበት ይመለስ’ ብለህ ለሕዝቡ ዐውጅ።” ስለዚህ ሃያ ሁለቱ ሺህ ሲመለሱ ዐሥሩ ሺህ ብቻ ቀሩ።

4. እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “አሁንም ሰዎቹ ብዙ ናቸው፤ ወደ ወንዝ ይዘሃቸው ውረድ፤ በዚያም እለይልሃለሁ። ‘ይህ ከአንተ ጋር ይሂድ’ የምለው፣ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ ነገር ግን፣ ‘ይህ ከአንተ ጋር አይሂድ’ የምለው፣ ከአንተ ጋር አይሄድም።”

5. ስለዚህ ጌዴዎን ሰዎቹን ወደ ወንዝ ይዞአቸው ወረደ፤ እዚያም እግዚአብሔር፤ “ውሻ በምላሱ እየጨለፈ እንደሚጠጣ ሁሉ፣ በምላሳቸው የሚጠጡትን፣ በጒልበታቸው ተንበርክከው ከሚጠጡት ለይ” አለው።

6. ሦስት መቶ ሰዎች ውሃውን በእጃቸው እያፈሱ ጠጡ፤ የቀሩት ሁሉ ግን ለመጠጣት በጒልበታቸው ተንበረከኩ።

7. እግዚአብሔርም ጌዴዎንን፣ “ውሃውን በእጃቸው እያፈሱ በጠጡት ሦስት መቶ ሰዎች አድናችኋለሁ፤ ምድያማውያንንም በእጃችሁ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ የቀሩት በሙሉ ወደየመጡበት ይመለሱ” አለው።

8. ጌዴዎንም የቀሩትን እስራኤላውያን በሙሉ ወደየድንኳናቸው እንዲመለሱ አደረገ፤ ሦስት መቶውን ግን አስቀራቸው፤ እነርሱም የሚመለሱትን ሰዎች ስንቅና መለከት ወሰዱ።በዚህ ጊዜ የምድያማውያኑ ሰፈር ከእነርሱ በታች በሸለቆአማው ውስጥ ነበር።

9. በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ተነሥ፤ በሰፈሩም ላይ ውረድ፤ በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁና።

10. አደጋ ለመጣል የምትፈራ ከሆነ ግን፣ ፉራ ከተባለው አገልጋይህ ጋር ወደ ሰፈሩ ውረድ፤

11. የሚሉትንም አድምጥ፤ ከዚያ በኋላ በሰፈሩ ላይ አደጋ ለመጣል ድፍረት ታገኛለህ፤” ስለዚህም ጌዴዎን አገልጋዩን ፉራን አስከትሎ እስከ ሰፈሩ ዳርቻ ወረደ።

12. ብዛታቸው እንደ አንበጣ መንጋ የሆነ ምድያማውያን፣ አማሌቃውያንና ሌሎችም የምሥራቅ ሕዝቦች በሸለቆው ውስጥ ሰፍረው ነበር፤ የግመሎቻቸውም ብዛት በባሕር ዳርቻ እንዳለ አሸዋ ስፍር ቍጥር አልነበረውም።

13. አንድ ሰው ያየውን ሕልም ለጓደኛው በሚነግርበት ጊዜ ጌዴዎን እዚያ ደረሰ። ያም ሰው፣ “በሕልሜ ክብ የሆነ አንድ የገብስ ቂጣ ከላይ ተንከባሎ በምድያማውያን ሰፈር ላይ ሲወርድ፣ ድንኳኑንም ሲመታው ከአመታቱም ኀይለኛነት የተነሣ ድንኳኑ ተገልብጦ ሲፈራርስ አየሁ” በማለት ይነግረው ነበር።

14. ጓደኛውም መልሶ፣ “ይህ የእስራኤላዊው የኢዮአስ ልጅ የጌዴዎን ሰይፍ እንጂ ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም፤ እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድያማውያንንና ሰፈሩን በሙሉ በእጁ አሳልፎ ሰጥቶታልና” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 7