ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 5:4-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. እንደ ገናም ከእነዚህ ጥቂት ወስደህ እሳት ውስጥ ጨምራቸው፤ አቃጥላቸውም። እሳትም ከዚያ ወጥቶ ወደ እስራኤል ቤት ሁሉ ይሰራጫል።

5. “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አገሮችን በዙሪያዋ ሁሉ አድርጌ፣ በአሕዛብም መካከል ያስቀመጥኋት ኢየሩሳሌም ይህች ናት።

6. እርስዋም በዙሪያዋ ካሉት አገሮችና አሕዛብ ይልቅ በሕጌና በሥርዐቴ ላይ በክፋቷ ዐመፀች፤ ሕጌን ጥላለች፤ ሥርዐቴንም አልተከተለችም።”

7. “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዙሪያችሁ ካሉት አሕዛብ ይልቅ ሞገደኞች ሆናችኋል፤ ሥርዐቴን አልተከተላችሁም፤ ለሕጌም አልታዘዛችሁም። በዙሪያችሁ የሚገኙ አሕዛብ የሚጠብቁትን ሕግ እንኳ አልጠበቃችሁም።

8. “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ፤ እኔ ራሴ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፤ በአሕዛብም ፊት ፍርድ አመጣብሻለሁ።

9. በጸያፍ ተግባርሽ ሁሉ ምክንያት ካሁን ቀደም ያላደረግሁትን፣ ወደ ፊትም የማላደርገውን በአንቺ ላይ አደርጋለሁ።

10. ስለዚህ በመካከልሽ አባቶች ልጆቻቸውን፣ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ፤ ፍርድንም አመጣብሻለሁ፤ ከአንቺ የተረፉትንም ለነፋስ እበትናለሁ።

11. ስለዚህ በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ መቅደሴን በረከሱ ምስሎችሽና በጸያፍ ተግባርሽ ሁሉ ስላጐደ ፍሽ፣ ፊቴን ከአንቺ እመልሳለሁ፤ በርኅራኄ አልመለከትሽም፤ አልምርሽም።

12. ከሕዝብሽ ሢሶው በቸነፈር ይሞታል፤ በመካከልሽም በራብ ያልቃል፤ ሌላው ሢሶ ከቅጥርሽ ውጪ በሰይፍ ይወድቃል፤ የቀረውን ሢሶ ደግሞ ለነፋስ እበትናለሁ፤ በተመዘዘም ሰይፍ አሳድደዋለሁ።

13. “ከዚያም ቍጣዬ ይበርዳል፤ በእነርሱ ላይ የመጣው መቅሠፍቴ ይመለሳል፤ ስበቀላቸው እረካለሁ፤ በእነርሱም ላይ መዓቴን ካወረድሁ በኋላ፣ እኔ እግዚአብሔር በቅናት እንደ ተናገርሁ ያውቃሉ።

14. “በዙሪያሽ ባሉ አሕዛብ መካከል፤ በአጠገብሽም በሚያልፉ ሁሉ ፊት ባድማና መሳለቂያ አደርግሻለሁ።

15. በቍጣና በመዓት፣ እንዲሁም በጭካኔ ፍርድ በማመጣብሽ ጊዜ፣ በዙሪያሽ ባሉ አሕዛብ ዘንድ የመሣቂያና የመሣለቂያ፣ የተግሣጽና የማስደንገጫ ምልክት ትሆኛለሽ። እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 5