ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 5:11-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ስለዚህ በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ መቅደሴን በረከሱ ምስሎችሽና በጸያፍ ተግባርሽ ሁሉ ስላጐደ ፍሽ፣ ፊቴን ከአንቺ እመልሳለሁ፤ በርኅራኄ አልመለከትሽም፤ አልምርሽም።

12. ከሕዝብሽ ሢሶው በቸነፈር ይሞታል፤ በመካከልሽም በራብ ያልቃል፤ ሌላው ሢሶ ከቅጥርሽ ውጪ በሰይፍ ይወድቃል፤ የቀረውን ሢሶ ደግሞ ለነፋስ እበትናለሁ፤ በተመዘዘም ሰይፍ አሳድደዋለሁ።

13. “ከዚያም ቍጣዬ ይበርዳል፤ በእነርሱ ላይ የመጣው መቅሠፍቴ ይመለሳል፤ ስበቀላቸው እረካለሁ፤ በእነርሱም ላይ መዓቴን ካወረድሁ በኋላ፣ እኔ እግዚአብሔር በቅናት እንደ ተናገርሁ ያውቃሉ።

14. “በዙሪያሽ ባሉ አሕዛብ መካከል፤ በአጠገብሽም በሚያልፉ ሁሉ ፊት ባድማና መሳለቂያ አደርግሻለሁ።

15. በቍጣና በመዓት፣ እንዲሁም በጭካኔ ፍርድ በማመጣብሽ ጊዜ፣ በዙሪያሽ ባሉ አሕዛብ ዘንድ የመሣቂያና የመሣለቂያ፣ የተግሣጽና የማስደንገጫ ምልክት ትሆኛለሽ። እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።

16. የሚገድለውንና አጥፊ የሆነውን የራብ ፍላጻ በእናንተ ላይ በምወረውርበት ጊዜ በእርግጥ ላጠፋችሁ እሰድዳለሁ። በራብ ላይ ራብ አመጣባችኋለሁ፤ የምግብ ምንጫችሁንም አደርቃለሁ።

17. ራብንና የዱር አራዊትን እሰድባችኋለሁ፤ እነርሱም ልጅ አልባ ያደርጓችኋል። ቸነፈርና ደም መፋሰስ ያጥለቀልቃችኋል፤ ሰይፍንም አመጣባችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 5