ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 45:6-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ‘ “ከተቀደሰው ስፍራ ጋር የተያያዘ ወርዱ አምስት ሺህ ክንድ፣ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ የሆነ ቦታ ለከተማዪቱ ርስት አድርገህ ስጥ፤ ይህም ለመላው የእስራኤል ቤት ይሆናል።

7. ‘ “ገዡ ከቅዱሱ ስፍራና ከከተማው ወሰን ግራና ቀኝ ርስት ይኖረዋል፤ ይህም ከምዕራብ በኩል ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ምሥራቅ በመዝለቅ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያለውን ወሰን ርዝመት ተከትሎ ለአንዱ ነገድ ከተሰጠው ርስት ጋር ጐን ለጐን ይሄዳል።

8. ይህም መሬት በእስራኤል ምድር የገዡ ርስት ይሆናል። ከእንግዲህ ገዦቼ ሕዝቤን አይጨቍኑም፤ ነገር ግን የእስራኤል ቤት በየነገዳቸው ርስት እንዲይዙ ይፈቅዱላቸዋል።

9. ‘ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የእስራኤል ገዦች ሆይ! ከልክ ዐልፋችኋል፤ ይብቃችሁ፤ ዐመፅንና ጭቈናን ተዉ፤ ቀናና ትክክል የሆነውን ነገር አድርጉ። የሕዝቤን ርስት መቀማት ይቅርባችሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

10. ትክክለኛ ሚዛን ትክክለኛ ኢፍና ትክክለኛ ባዶስ ይኑራችሁ።

11. የኢፍና የባዶሱ መመዘኛ ተመሳሳይ ይሁን፤ አንድ ባዶስ የሆመር አንድ ዐሥረኛ እንዲሁም አንድ ኢፍ የሆመር አንድ ዐሥረኛ ይሆናል፤ ሆመር ለሁለቱም ሚዛኖች መደበኛ መለኪያ ነው።

12. አንድ ሰቅል ሃያ ጌራህ የሚይዝ ይሆናል፤ በሃያ ሰቅል ላይ ሃያ አምስት ሰቅልና ዐሥራ አምስት ሰቅል ሲጨመር አንድ ምናን ይሆናል።’

13. ‘ “የምታቀርቡት ልዩ መባ ይህ ነው፤ ከአንድ ሆመር መስፈሪያ ስንዴ አንድ ስድስተኛ ኢፍ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ሆመር ገብስ አንድ ስድስተኛ ኢፍ ነው።

14. ዘይቱ በባዶስ ሲለካ የተወሰነው መስፈሪያ ከእያንዳንዱ ሆመር አንድ ዐሥረኛ ባዶስ ይሆናል፤ ይኸውም ዐሥር ባዶስ ወይም አንድ ሆመር ነው፤ ዐሥር ባዶስ ከአንድ ሆመር ጋር እኩል ነውና።

15. እንዲሁም ውሃ ከጠገበው ከእስራኤል መሰማሪያ፣ ሁለት መቶ በግ ካለው ከእያንዳንዱ መንጋ አንድ በግ ይውሰድ። ይህ ሁሉ ለሕዝቡ ማስተስረያ ለሚሆነው ለእህል ቍርባን፣ ለሚቃጠል መሥዋዕትና ለኅብረት መሥዋዕት ይውላል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

16. የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ ይህን ልዩ መባ ለእስራኤል ገዥ ይሰጣሉ።

17. በበዓላት፣ በወር መባቻና በሰንበታት፣ ለእስራኤል ቤት በተወሰኑት በዓላት ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባንና የመጠጥ ቍርባን ማቅረብ የገዡ ኀላፊነት ነው፤ ለእስራኤል ቤት ማስተስረያ እንዲሆንም የኀጢአት መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባን፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ያቀርባል።’

18. “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በመጀመሪያው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን ነውር የሌለበትን ወይፈን ውሰድ፤ መቅደሱንም አንጻው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 45