ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 45:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ‘ “ምድሪቱን ርስት አድርጋችሁ በዕጣ በምትከፋፈሉበት ጊዜ፣ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ፣ ወርዱ ሃያ ሺህ ክንድ የሆነውን አንዱን ክፍል፣ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ስፍራ አድርጋችሁ ስጡ፤ ስፍራውም በሙሉ ቅዱስ ይሆናል፤

2. ከዚሁም አምስት መቶ ክንድ በአምስት መቶ ክንድ፣ ዙሪያው አምሳ ክንድ ባዶ ቦታ ቀርቶ፣ ለመቅደሱ ይሁን።

3. ከተቀደሰውም ስፍራ ላይ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ፣ ወርዱም ዐሥር ሺህ ክንድ ለካ፤ በዚህም ውስጥ መቅደሱ፣ ይኸውም ቅድስተ ቅዱሳኑ ይሆናል።

4. ይህም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለሚያገለግሉና፣ በእግዚአብሔር ፊት ለአገልግሎት ለሚቀርቡ ካህናት፣ ቅዱስ የሆነ የምድሪቱ ክፍል ይሆናል።

5. ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ፣ ወርዱ ዐሥር ሺህ ክንድ ስፋት ያለው ስፍራ መኖሪያ ከተሞቻቸውን እንዲከትሙ በቤተ መቅደስ ለሚያገለግሉ ሌዋውያን ርስት ይሆናል።

6. ‘ “ከተቀደሰው ስፍራ ጋር የተያያዘ ወርዱ አምስት ሺህ ክንድ፣ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ የሆነ ቦታ ለከተማዪቱ ርስት አድርገህ ስጥ፤ ይህም ለመላው የእስራኤል ቤት ይሆናል።

7. ‘ “ገዡ ከቅዱሱ ስፍራና ከከተማው ወሰን ግራና ቀኝ ርስት ይኖረዋል፤ ይህም ከምዕራብ በኩል ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ምሥራቅ በመዝለቅ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ያለውን ወሰን ርዝመት ተከትሎ ለአንዱ ነገድ ከተሰጠው ርስት ጋር ጐን ለጐን ይሄዳል።

8. ይህም መሬት በእስራኤል ምድር የገዡ ርስት ይሆናል። ከእንግዲህ ገዦቼ ሕዝቤን አይጨቍኑም፤ ነገር ግን የእስራኤል ቤት በየነገዳቸው ርስት እንዲይዙ ይፈቅዱላቸዋል።

9. ‘ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የእስራኤል ገዦች ሆይ! ከልክ ዐልፋችኋል፤ ይብቃችሁ፤ ዐመፅንና ጭቈናን ተዉ፤ ቀናና ትክክል የሆነውን ነገር አድርጉ። የሕዝቤን ርስት መቀማት ይቅርባችሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

10. ትክክለኛ ሚዛን ትክክለኛ ኢፍና ትክክለኛ ባዶስ ይኑራችሁ።

11. የኢፍና የባዶሱ መመዘኛ ተመሳሳይ ይሁን፤ አንድ ባዶስ የሆመር አንድ ዐሥረኛ እንዲሁም አንድ ኢፍ የሆመር አንድ ዐሥረኛ ይሆናል፤ ሆመር ለሁለቱም ሚዛኖች መደበኛ መለኪያ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 45