ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 41:11-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ከክፍቱ ቦታ ግራና ቀኝ ወዳሉ ክፍሎች የሚያስገቡ በሮች ነበሩ። አንዱ በሰሜን በኩል ሲሆን፣ ሌላው በር ደግሞ በደቡብ በኩል ነው። ክፍቱን ቦታ ዙሪያውን የሚያገናኘው መሠረት ስፋቱ አምስት ክንድ ነው።

12. በምዕራብ በኩል ከቤተ መቅደሱ ግቢ ትይዩ የሆነው ሕንጻ ወርድ ሰባ ክንድ ነበር። የሕንጻው ግንብ ውፍረት ዙሪያውን አምስት ክንድ ሲሆን፣ ርዝመቱ ዘጠና ክንድ ነበር።

13. ከዚያም ቤተ መቅደሱን ለካ፤ ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ ሲሆን፣ የቤተ መቅደሱ ግቢና ሕንጻ ከነግንቡ ደግሞ አንድ መቶ ክንድ ሆነ።

14. በምሥራቅ በኩል የቤተ መቅደሱ ግቢ ስፋት፣ ከቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ያለውን ስፍራ ጨምሮ አንድ መቶ ክንድ ነበር።

15. ከዚያም ከቤተ መቅደሱ በስተ ጀርባ ከግቢው ትይዩ ያለውን ሕንጻ ለካ፤ ይህም በግራና በቀኝ ያሉትን መተላለፊያዎች የሚጨምር ሲሆን፣ ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ ነበር።የውጩ መቅደስና የውስጡ መቅደስ ከአደባባዩ ትይዩ ያለው መተላለፊያ በረንዳ፣

16. እንዲሁም መድረኮቹና ጠበብ ያሉት መስኮቶች፣ በሦስቱም ዙሪያ ያሉት መተላለፊያዎች፣ ከመድረኩ በላይና ራሱ መድረኩም ጭምር ሁሉም በዕንጨት ተለብዶ ነበር። ወለሉ፣ እስከ መስኮቶቹ ያለው ግንብና መስኮቶቹ ተለብደዋል።

17. ከውስጡ መቅደስ መግቢያ በላይ ያለው ውስጡና ውጩ እንዲሁም በውስጡ መቅደስና በውጩ መቅደስ መካከል ያለው ሁሉ ዙሪያውን

18. ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ ተቀርጸውበት ነበር፤ የዘንባባ ዛፎቹ የተቀረጹት በኪሩብና በኪሩብ መካከል ነበር። እያንዳንዱም ኪሩብ ሁለት ፊት ነበረው፤

19. የሰው ፊት ያለው ኪሩብ በአንድ በኩል ወዳለው ዘንባባ የዞረ ሲሆን፣ የአንበሳ ፊት ያለውም በሌላ በኩል ወዳለው ዘንባባ ዞሮ ነበር። ሁሉም በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ላይ ተቀርጸው ነበር።

20. ከወለሉ አንሥቶ ከመግቢያው በላይ እስካለው ስፍራ ድረስ፣ የውስጡ መቅደስ የውጭ ግድግዳ ላይ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾአል።

21. የውስጡ መቅደስ በር መቃን ባለ አራት ማእዘን ነበር፤ ከቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት ለፊት ያለው በር እንዲሁ ባለ አራት ማእዘን ነበር።

22. ሦስት ክንድ ቁመት፣ ሁለት ክንድ ወርድ፣ ሁለት ክንድ ርዝመት ያለው የዕንጨት መሠዊያ ነበር፤ ማእዘኖቹ፣ መሠረቱና ጐኖቹ ሁሉ ከዕንጨት የተሠሩ ነበሩ። ሰውዬውም፣ “ይህች በእግዚአብሔር ፊት ያለች ገበታ ናት” አለኝ።

23. የውስጡ መቅደስና ቅድስተ ቅዱሳኑ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት በር አላቸው፤

24. እያንዳንዱ በር መካከሉ ላይ በመታጠፊያ የተያያዙ መዝጊያዎች አሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 41