ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 31:5-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ስለዚህ በደን ካሉት ዛፎች ሁሉ፣እጅግ ከፍ አለ፤ቅርንጫፎቹ በዙ፤ቀንበጦቹ ረዘሙ፤ከውሃውም ብዛት የተነሣ ተስፋፉ።

6. የሰማይ ወፎች ሁሉ፣በቅርንጫፎቹ ላይ ጐጆአቸውን ሠሩ፤የምድር አራዊት ሁሉ፣ከቅርንጫፎቹ ሥር ግልገሎቻቸውን ወለዱ።ታላላቅ መንግሥታትም ሁሉ፣ከጥላው ሥር ኖሩ።

7. ከተንሰራፉት ቅርንጫፎቹ ጋር፣ውበቱ ግሩም ነበር፤ብዙ ውሃ ወዳለበት፣ሥሮቹ ጠልቀው ነበርና።

8. በእግዚአብሔር ገነት ያሉ ዝግባዎች፣ሊወዳደሩት አልቻሉም፤የጥድ ዛፎች፣የእርሱን ቅርንጫፎች አይተካከሉትም፤የአስታ ዛፎችም፣ከእርሱ ቅርንጫፎች ጋር አይወዳደሩም፤በእግዚአብሔር ገነት ያለ ማናቸውም ዛፍ፣በውበት አይደርስበትም።

9. በብዙ ቅርንጫፎች፣ውብ አድርጌ ሠራሁት፤በእግዚአብሔርም የአትክልት ቦታ፣በገነት ያሉትን ዛፎች የሚያስቀና አደረግሁት።

10. “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጥቅጥቅ ባለው ቅጠል ላይ ጫፉን ከፍ በማድረግ ራሱን በማንጠራራቱ፣ በርዝማኔውም በመኵራራቱ፣

11. እንደ ክፋቱ መጠን የሥራውን ይከፍለው ዘንድ፣ ለአሕዛብ ገዥ አሳልፌ ሰጠሁት። አውጥቼ ጥየዋለሁ፤

12. ከአሕዛብ ወገን እጅግ ጨካኝ የሆኑትም ባዕዳን ሰዎች ቈራርጠው ጣሉት። ቀንበጦቹ በተራራዎቹና በሸለቆዎቹ ሁሉ ላይ ወድቀዋል፤ ቅርንጫፎቹም በውሃ መውረጃዎቹ ሁሉ ላይ ተሰባብረው ወድቀዋል፤ የምድሪቱ ሰዎች ሁሉ ከጥላው ሥር በመውጣት ትተውት ሄደዋል።

13. የሰማይ ወፎች ሁሉ በወደቀው ዛፍ ላይ ሰፈሩ፤ የምድር አራዊት ሁሉ በወደቀው ዛፍ ቅርንጫፎች ላይ ሰፈሩ።

14. ስለዚህ በውሃ አጠገብ ያለ ማንኛውም ዛፍ፣ ጫፎቹን ችምችም ካለው ቅጠል በላይ ከፍ በማድረግ፣ ከእንግዲህ ራሱን በትዕቢት አያንጠራራም። ከእንግዲህ ውሃ በሚገባ ያገኘ ማንኛውም ዛፍ ወደዚህ ዐይነቱ ከፍታ አይደርስም። ሁሉም ከምድር በታች ወደ ጒድጓድ ከሚወርድ ሟች ጋር አብሮ እንዲሞት ተወስኖበታልና።”

15. “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ወደ መቃብር በወረደበት ቀን ጥልቅ ምንጮችን ስለ እርሱ በሐዘን ሸፈንኋቸው፤ ወንዞቹን ገታሁ፤ ታላላቅ ፈሳሾችም ተቋረጡ። በእርሱም ምክንያት ሊባኖስን ጨለማ አለበስሁ፤ የደን ዛፎችም ሁሉ ደረቁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 31