ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 27:21-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. “ ‘የዐረብና የቄዳር መሳፍንት ሁሉ ደምበኞችሽ ነበሩ፤ ጠቦትና አውራ በግ፣ ፍየልም አምጥተው ከአንቺ ጋር ይገበያዩ ነበር።

22. “ ‘የሳባና የራዕማ ነጋዴዎች ከአንቺ ጋር ይገበያዩ ነበር፤ ምርጥ የሆነውን የሽቱ ቅመም ዐይነት ሁሉ፣ የከበረ ድንጋይና ወርቅ በማቅረብ በሸቀጥሽ ይለውጡ ነበር።

23. “ ‘ካራን፣ ካኔ፣ ዔደን፣ የሳባ ነጋዴዎች፣ አሦርና ኪልማድ ከአንቺ ጋር የንግድ ልውውጥ ያደርጉ ነበር።

24. እነዚህም በገበያሽ ውስጥ ያማረ ልብስ፣ ሰማያዊ ካባ፣ ወርቀ ዘቦ እንዲሁም በኅብረ ቀለም ያሸበረቀና በጥብቅ የተታታ ስጋጃ በማቅረብ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር።

25. “ ‘የተርሴስ መርከቦች፣ሸቀጥሽን አጓጓዙልሽ፤በባሕር መካከልም፣በከባድ ጭነት ተሞልተሽ ነበር።

26. ቀዛፊዎችሽ፣ወደ ጥልቁ ባሕር ይወስዱሻል፤የምሥራቁ ነፋስ ግን፣በባሕሩ መካከል ይሰባብርሻል።

27. የመርከብ አደጋ በሚደርስበሽ ቀን፣ሀብትሽ፣ ሸቀጥሽና የንግድ ዕቃሽ፣መርከብ ነጂዎችሽ፣ መርከበኞችሽና መርከብ ሠሪዎችሽ፣ነጋዴዎችሽና ወታደሮችሽ ሁሉ፣በመርከብ ላይ ያሉትም ሁሉ፣ወደ ባሕሩ ወለል ይዘቅጣሉ።

28. መርከበኞችሽ ሲጮኹ፣የባሕሩ ጠረፍ ይናወጣል።

29. ቀዛፊዎች ሁሉ፣መርከባቸውን ጥለው ይሄዳሉ፤መርከብ ነጂዎችና መርከበኞችም ሁሉ፣ወርደው ባሕሩ ዳር ይቆማሉ፤

30. ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፣በምሬት ያለቅሱልሻል፤በራሳቸውም ላይ ዐቧራ ነስንሰው፣በዐመድ ላይ ይንከባለላሉ።

31. ስለ አንቺ ጠጒራቸውን ይላጫሉ፤ማቅም ይለብሳሉ፤በነፍስ ምሬት፣በመራራም ሐዘን ያለቅሱልሻል።

32. ስለ አንቺ በዋይታ ያለቅሳሉ፤እንዲህም እያሉ ሙሾ ያወርዳሉ፤“ባሕር ውጦት የቀረ፣እንደ ጢሮስ ማን አለ?”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 27