ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 22:12-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. በመካከልሽ ያሉ ሰዎች ደም ለማፍሰስ ጒቦ ይቀበላሉ፤ አንቺም ዐራጣና ከፍተኛ ወለድ በመውሰድ ከባልንጀራሽ የማይገባ ትርፍ ዘረፍሽ፤ እኔንም ረስተሻል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

13. “ ‘ያለ አግባብ ባገኘሽው ጥቅምና በመካከልሽ ባፈሰስሽው ደም ላይ እጄን አጨበጭባለሁ።

14. እኔ ልቀጣሽ በምነሣበት ጊዜ በልበ ሙሉነት መቆም ትችያለሽን? ወይስ እጅሽ ሊበረታ ይችላልን? እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ አደርገዋለሁም።

15. በሕዝቦች መካከል እበትንሻለሁ፤ በየአገሩም እዘራሻለሁ፤ ከርኵሰትሽም አጠራሻለሁ።

16. በሕዝቦች ዘንድ በምትረክሺበት ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቂያለሽ።’ ”

17. የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

18. “የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት የብረት ዝቃጭ ሆነብኝ፤ ሁሉም በከውር ውስጥ ቀልጦ እንደሚቀር መዳብ፣ ቈርቈሮ፣ ብረትና እርሳስ ናቸው፤ እነዚህ ከብር የሚወጡ ዝቃጭ ናቸው።

19. ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ ‘ሁላችሁም የብረት ዝቃጭ ስለ ሆናችሁ ወደ ኢየሩሳሌም እሰበስባችኋለሁ።

20. ሰው ብርንና መዳብን፣ ብረትንና እርሳስን እንዲሁም ቈርቈሮን ለማቅለጥ በከውር ውስጥ አስገብቶ እሳት እንደሚያነድበት፣ እኔም እንደዚሁ በቍጣዬና በመዓቴ ወደ ከተማዪቱ እሰበስባችኋለሁ፤ በዚያም አቀልጣችኋለሁ።

21. ሰብስቤአችሁ የቍጣዬን እሳት በእስትንፋሴ አነድባችኋለሁ፤ እናንተም በዚያ ውስጥ ቀልጣችሁ ትቀራላችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ቍጣዬን በላያችሁ እንዳፈሰስሁ ታውቃላችሁ።

22. ብር በከውር ውስጥ እንደሚቀልጥ፣ እናንተም በከተማዋ ውስጥ ትቀልጣላችሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር ቍጣዬን በላያችሁ እንዳፈሰስሁ ታውቃላችሁ።’ ”

23. የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

24. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ምድሪቱን፣ ‘አንቺ ያልነጻሽ በቍጣም ቀን ዝናብ ያላገኘሽ ምድር ነሽ’ በላት።

25. መሳፍንቷ እያገሣ ግዳዩን እንደሚቦጫጭቅ አንበሳ በውስጧ ያሤራሉ፤ ሕዝቡን ይበላሉ፤ ንብረትንና የከበሩ ነገሮችን ይነጥቃሉ፤ ብዙዎችንም ሴቶች መበለት ያደርጋሉ።

26. ካህናቷ በሕጌ ላይ ያምፃሉ፤ ንዋያተ ቅድሳቴን ያረክሳሉ፤ የተቀደሰውን ከረከሰው አይለዩም፤ በጐደፈውና በንጹሑ መካከል ልዩነት እንደሌለ ያስተምራሉ፤ ሰንበታቴን ከማክበር ዘወር ብለዋል፤ በዚህም በመካከላቸው ተንቄአለሁ።

27. በውስጧ የሚገኙ መኳንንቷ ግዳይ እንደሚቦጫጭቁ ተኵላዎች ናቸው፤ በግፍ ትርፍ ለመሰብሰብ ደም ያፈሳሉ፤ ሕይወትም ያጠፋሉ።

28. ነቢያቷም በሐሰት ራእይና በውሸት ሟርት ይህን ሁሉ ድርጊት ያድበሰብሱላቸዋል፤ እግዚአብሔርም ሳይናገር፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ይላሉ።

29. በምድሪቱ የሚኖረው ሕዝብ ይቀማል፤ ይዘርፋል፤ ፍትሕ በማጒደልም ድኻውንና ችግረኛውን ይጨቍናል፤ መጻተኛውንም ይበድላል።

30. “ምድሪቱን እንዳላጠፋት ቅጥሩን የሚጠግን፣ በፈረሰውም በኩል በፊቴ የሚቆምላት ሰው ከመካከላቸው ፈለግሁ፤ ነገር ግን አንድም አላገኘሁም።

31. ስለዚህ መዓቴን አፈስባቸዋለሁ፤ በጽኑ ቍጣዬም አነዳቸዋለሁ፤ ያደረጉትንም በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር”።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 22