ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 4:6-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. እንዲሁም ዐሥር የመታጠቢያ ገንዳዎች አሠርቶ አምስቱን በደቡብ፣ አምስቱን ደግሞ በሰሜን በኩል አስቀመጠ፤ ገንዳዎች ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡት ነገሮች የሚታጠቡባቸው ሲሆኑ፣ በርሜሉ ግን ለካህናት መታጠቢያ የሚያገለግል ነበር።

7. በተሰጠው የአሠራር መመሪያ መሠረት፣ ዐሥር የወርቅ መቅረዞች ሠርቶ ወደ ቤተ መቅደሱ በማስገባት፣ አምስቱን በስተ ደቡብ፣ አምስቱን በስተ ሰሜን አኖራቸው።

8. ዐሥር ጠረጴዛ ሠርቶም ወደ ቤተ መቅደሱ በማስገባት አምስቱን በስተ ደቡብ፣ አምስቱን ደግሞ በስተ ሰሜን በኩል አኖራቸው፤ ደግሞም አንድ መቶ ጐድጓዳ የወርቅ ሳሕኖች ሠራ።

9. የካህናቱንም አደባባይ ሠራ፣ እንዲሁም ታላቁን አደባባይና በሮቹን ከሠራ በኋላ በናስ ለበጣቸው።

10. በርሜሉንም ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ ምሥራቅ ባለው ማዕዘን በቀኝ በኩል አኖረው።

11. እንዲሁም ምንቸቱን፣ መጫሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን ሠራ። ኪራምም ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት የሚውሉትን ዕቃዎች ለንጉሥ ሰሎሞን ሠርቶ ጨረሰ፤ እነዚህም

12. ሁለቱ ዐምዶች፣በአዕማዱ ጫፍ ላይ ያሉት ሁለት ባለ ሳሕን ቅርጽ ጒልላት በዐምዶቹ ላይ ያሉትን ሁለቱን፣ባለ ሳሕን ቅርጽ ጒልላት የሚያስጌጡ ሁለት ዙር መርበቦች፤

13. በዐምዶቹ ላይ ያሉትን ሁለቱን፣ ባለ ሳሕን ቅርጽ ጒልላት እንዲያስጌጡ ለያንዳንዱ መርበብ ሁለት ዙር ሮማኖች ለሁለቱም ዙር መርበቦች በድምሩ አራት መቶ ሮማኖች፤

14. መቆሚያዎች ከነመታጠቢያ ሳሕኖቻቸው፤

15. በርሜሉና እርሱን የተሸከሙት ዐሥራ ሁለት ኮርማዎች፤

16. ምንቸቶችና መጫሪያዎች፣ሜንጦዎችና ከነዚሁም ጋር የተያያዙ ዕቃዎች።ኪራምአቢ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገልገያ እንዲሆን ለሰሎሞን የሠራቸው ዕቃዎች በሙሉ ከተወለወለ ናስ የተሠሩ ነበሩ።

17. ንጉሡም እነዚህ ዕቃዎች በዮርዳኖስ ሸለቆ፣ በሱኮትና በጽሬዳ መካከል ባለው በሸክላ ዐፈር ቦታ ቀልጠው በሸክላ ቅርጽ ተሠርተው እንዲወጡ አደረገ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 4