ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 32:5-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. ከዚህ በኋላም ንጉሡ ጠንክሮ በመሥራት፣ ከቅጥሩ የፈራረሱትን ሁሉ ጠገነ፤ በላዩም ማማ ሠራበት፤ በውጭ በኩልም ሌላ ቅጥር በመገንባት የዳዊትን ከተማ ድጋፍ እርከን አጠናከረ፤ እንደዚሁም ብዙ የጦር መሣሪያዎችንና ጋሻዎችን ሠራ።

6. የጦር መኮንኖችንም በሕዝቡ ላይ ሾሞ በከተማዪቱ በር አደባባይ ላይ በፊቱ ከሰበሰበ በኋላ እንዲህ ሲል አበረታታቸው፤

7. “በርቱ፤ጠንክሩ፤ ከእኛ ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ስለሚበልጥ፣ የአሦርን ንጉሥና አብሮት ያለውን ብዙ ሰራዊት አትፍሩ፤ አትደንግጡም።

8. ከእነርሱ ጋር ያለው የሥጋ ክንድ ሲሆን፣ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና ጠላታችንን የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው።” ሕዝቡም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በተናገረው ቃል ተበረታታ።

9. ከዚህ በኋላ ሰናክሬም ከሰራዊቱ ሁሉ ጋር ለኪሶን ከቦ ሳለ፣ የሚከተለውን መልእክት በጦር መኮንኖቹ አማካይነት፣ ለሕዝቅያስና ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ለነበሩት ለይሁዳ ሕዝብ ላከ፤

10. “የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የሚለው ይህ ነው፤ በተከበበችው በኢየሩሳሌም እስከዚህ የቈያችሁት በማን ተማምናችሁ ነው?

11. ሕዝቅያስ፣ ‘አምላካችን እግዚአብሔር ከአሦር ንጉሥ እጅ ያድነናል’ ማለቱስ በራብና በጥማት እንድትሞቱ ሊያስታችሁ አይደለምን?

12. ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም፣ ‘በአንድ መሠዊያ ፊት ስገዱ፤ በላዩም መሥዋዕት አቃጥሉ’ በማለት የራሱን አምላክ የኰረብታ መስገጃ ስፍራዎችንና መሠዊያዎችን ያስወገደስ ሕዝቅያስ አይደለምን?

13. “እኔና አባቶቼ በሌሎች አገሮች ሕዝቦች ሁሉ ላይ ያደረግነውን አታውቁምን? ታዲያ የእነዚያ መንግሥታት አማልክት ምድራቸውን ከእጄ ለማዳን ችለዋልን?

14. አባቶቼ ካጠፏቸው ከእነዚህ የመንግሥታት አማልክት ሁሉ፣ ሕዝቡን ከእጄ ሊያድን የቻለ ከእነዚህ አምላክ የትኛው ነው? ታዲያ አምላካችሁ እንዴት ከእጄ ሊያድናችሁ ይችላል?

15. አሁንም ሕዝቅያስ በዚህ ዐይነት አያታልላችሁ፤ አያስታችሁም። የየትኛውም አገር ሕዝብ ወይም መንግሥት አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ወይም ከአባቶቼ እጅ መታደግ የቻለ ስለሌለ አትመኑት። የእናንተ አምላክማ ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ ምንኛ ያንስ!”

16. የሰናክሬም ሹማምትም በእግዚአብሔር አምላክና በባሪያው በሕዝቅያስ ላይ ከዚህ የከፋ ብዙ ነገር ተናገሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 32