ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 32:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሕዝቅያስ እንዲህ ባለ ታማኝነት ነገሮችን ሁሉ ካከናወነ በኋላ፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ይሁዳን ወረረ። ድል አድርጎ የራሱ ሊያደርጋቸው በማሰብም የተመሸጉትን ከተሞች ከበበ።

2. ሕዝቅያስም ሰናክሬም መምጣቱንና ኢየሩሳሌምንም ለመውጋት ማሰቡን ባወቀ ጊዜ፣

3. ከከተማዪቱ ውጭ ያሉት የውሃ ምንጮች እንዲዘጉ ከሹማምቱና ከጦር አለቆቹ ጋር ተማከረ፤ እነርሱም ረዱት።

4. ብዙ ሰዎችም ተሰብስበው “የአሦር ነገሥታት መጥተው ስለ ምን ብዙ ውሃ ያገኛሉ?” በማለት ምንጮቹን ሁሉና በምድር ውስጥ ለውስጥ ይተላለፍ የነበረውን ውሃ ዘጉ።

5. ከዚህ በኋላም ንጉሡ ጠንክሮ በመሥራት፣ ከቅጥሩ የፈራረሱትን ሁሉ ጠገነ፤ በላዩም ማማ ሠራበት፤ በውጭ በኩልም ሌላ ቅጥር በመገንባት የዳዊትን ከተማ ድጋፍ እርከን አጠናከረ፤ እንደዚሁም ብዙ የጦር መሣሪያዎችንና ጋሻዎችን ሠራ።

6. የጦር መኮንኖችንም በሕዝቡ ላይ ሾሞ በከተማዪቱ በር አደባባይ ላይ በፊቱ ከሰበሰበ በኋላ እንዲህ ሲል አበረታታቸው፤

7. “በርቱ፤ጠንክሩ፤ ከእኛ ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ስለሚበልጥ፣ የአሦርን ንጉሥና አብሮት ያለውን ብዙ ሰራዊት አትፍሩ፤ አትደንግጡም።

8. ከእነርሱ ጋር ያለው የሥጋ ክንድ ሲሆን፣ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳንና ጠላታችንን የሚዋጋልን አምላካችን እግዚአብሔር ነው።” ሕዝቡም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ በተናገረው ቃል ተበረታታ።

9. ከዚህ በኋላ ሰናክሬም ከሰራዊቱ ሁሉ ጋር ለኪሶን ከቦ ሳለ፣ የሚከተለውን መልእክት በጦር መኮንኖቹ አማካይነት፣ ለሕዝቅያስና ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም ለነበሩት ለይሁዳ ሕዝብ ላከ፤

10. “የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የሚለው ይህ ነው፤ በተከበበችው በኢየሩሳሌም እስከዚህ የቈያችሁት በማን ተማምናችሁ ነው?

11. ሕዝቅያስ፣ ‘አምላካችን እግዚአብሔር ከአሦር ንጉሥ እጅ ያድነናል’ ማለቱስ በራብና በጥማት እንድትሞቱ ሊያስታችሁ አይደለምን?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 32