ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 29:25-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. ንጉሥ ሕዝቅያስም በዳዊት፣ በንጉሡ ባለ ራእይ በጋድና በነቢዩ በናታን በተሰጠው መመሪያ መሠረት ሌዋውያኑን ጸናጽል፣ በገናና መሰንቆ አስይዞ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መደባቸው፤ ይህም በነቢያት አማካይነት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ትእዛዝ ነበር።

26. ስለዚህ ሌዋውያኑ የዳዊትን የዜማ ዕቃዎች፣ ካህናቱም መለከቶቻቸውን ይዘው ዝግጁ በመሆን ቆሙ።

27. ከዚህ በኋላ ሕዝቅያስ የሚቃጠለው መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ እንዲቀርብ አዘዘ። መሥዋዕቱ ማረግ በጀመረ ጊዜም፣ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት የዜማ ዕቃዎችና በመለከት የታጀበ ዝማሬም ጀመረ።

28. መዘምራኑ በሚዘም ሩበትና መለከተኞቹም በሚነፉበት ጊዜም መላው ጉባኤ አጎንብሰው ሰገዱ፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት እስኪጠናቀቅ ድረስም ይህ ሁሉ ቀጠለ።

29. መሥዋዕቱ ሁሉ ቀርቦ ካበቃ በኋላ፣ ንጉሡና አብረውት የነበሩት ሁሉ ተንበርክከው ሰገዱ።

30. ንጉሥ ሕዝቅያስና ሹማምቱ፣ ሌዋውያኑ በዳዊትና በባለ ራእዩ በአሳፍ ቃል እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ አዘዙ። እነርሱም ውዳሴውን በደስታ ዘመሩ፤ ራሳቸውንም አጎንብሰው ሰገዱ።

31. ከዚያም ሕዝቅያስ፣ “እነሆ፤ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ቀድሳችኋል፤ አሁንም ቅረቡ፤ መሥዋዕትና የምስጋና ስጦታ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ጉባኤው መሥዋዕትና የምስጋና ስጦታ አመጡ፤ ልባቸው የፈቀደ ሁሉም የሚቃጠል መሥዋዕት አመጡ።

32. ጉባኤውም ያመጣው የሚቃጠለው መሥዋዕት ብዛት ሰባ ወይፈኖች፣ መቶ አውራ በጎችና ሁለት መቶ ተባዕት የበግ ጠቦቶች ናቸው፤ ሁሉም የሚቃጠል መሥዋዕት ሆነው ለእግዚአብሔር የሚቀርቡ ነበሩ።

33. ለመሥዋዕት የተቀደሱት እንስሳት ባጠቃላይ ስድስት መቶ ወይፈን፣ ሦስት ሺህ በጎችና ፍየሎች ነበሩ።

34. ይሁን እንጂ ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ቈዳ ሁሉ ለመግፈፍ ቊጥራቸው እጅግ ጥቂት ነበር፤ ስለዚህ ወገኖቻቸው የሆኑት ሌዋውያን ሥራው እስኪያልቅና ሌሎች ካህናት እስኪቀደሱ ድረስ ረዷቸው፤ ሌዋውያኑም ራሳቸውን ለመቀደስ ከካህናቱ ይልቅ ጠንቃቆች ነበሩና።

35. ከሚቃጠለው መሥዋዕት ጋር የሚቀርበውን የኅብረት መሥዋዕት ስብና የመጠጡን ቍርባን ጨምሮ የሚቃጠለው መሥዋዕት እጅግ ብዙ ነበር። በዚህ ሁኔታም የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት እንደ ገና ተደራጀ።

36. ሕዝቅያስና ሕዝቡ ነገሩ ሁሉ እንዲህ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲከናወን እግዚአብሔር ስለረዳቸው ሐሴት አደረጉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 29