ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 29:18-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ከዚያም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ገብተው እንዲህ አሉ፤ “የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በሙሉ፣ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ከነዕቃዎቹ ሁሉ፣ ኀብስተ ገጹ የሚቀመጥበትን ጠረጴዛ፣ ከነዕቃዎቹ አንጽተናል።

19. ንጉሥ አካዝ ነግሦ ሳለ ታማኝነቱን ትቶ፣ ከቦታቸው ያነሣቸውን ዕቃዎች ሁሉ አዘጋጅተን ቀድሰናቸዋል፤ እነሆ፤ ዕቃዎቹ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠዊያ ፊት ለፊት ናቸው።”

20. በማግስቱም ጧት በማለዳ፣ ንጉሥ ሕዝቅያስ የከተማዪቱን ሹማምት በአንድነት ሰብስቦ፣ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጣ፤

21. እነርሱም ስለ መንግሥቱ፣ ስለ መቅደሱና ስለ ይሁዳ ሰባት ወይፈኖች፣ ሰባት አውራ በጎች፣ ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና ሰባት ተባዕት የፍየል ጠቦቶች ለኀጢአት መሥዋዕት አቀረቧቸው፤ ንጉሡም እነዚህን በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ እንዲያቀርቡ የአሮንን ዘሮች ካህናቱን አዘዘ።

22. ካህናቱም ወይፈኖቹን ዐርደው ደሙን በመውሰድ በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ አውራ በጎቹንም ዐርደው ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ እንደዚሁም ጠቦቶቹን ዐርደው ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩት።

23. ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆኑትን ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቡ፤ እነርሱም እጆቻቸውን ጫኑባቸው።

24. ንጉሡ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኀጢአት መሥዋዕት ስለ እስራኤል ሁሉ እንዲቀርብ አዞ ስለ ነበር፣ ካህናቱ ፍየሎቹን ዐርደው ስለ እስራኤል ሁሉ ማስተስረያ እንዲሆን የኀጢአት መሥዋዕት በማድረግ ደሙን በመሠዊያው ላይ አቀረቡ።

25. ንጉሥ ሕዝቅያስም በዳዊት፣ በንጉሡ ባለ ራእይ በጋድና በነቢዩ በናታን በተሰጠው መመሪያ መሠረት ሌዋውያኑን ጸናጽል፣ በገናና መሰንቆ አስይዞ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መደባቸው፤ ይህም በነቢያት አማካይነት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ትእዛዝ ነበር።

26. ስለዚህ ሌዋውያኑ የዳዊትን የዜማ ዕቃዎች፣ ካህናቱም መለከቶቻቸውን ይዘው ዝግጁ በመሆን ቆሙ።

27. ከዚህ በኋላ ሕዝቅያስ የሚቃጠለው መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ እንዲቀርብ አዘዘ። መሥዋዕቱ ማረግ በጀመረ ጊዜም፣ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት የዜማ ዕቃዎችና በመለከት የታጀበ ዝማሬም ጀመረ።

28. መዘምራኑ በሚዘም ሩበትና መለከተኞቹም በሚነፉበት ጊዜም መላው ጉባኤ አጎንብሰው ሰገዱ፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት እስኪጠናቀቅ ድረስም ይህ ሁሉ ቀጠለ።

29. መሥዋዕቱ ሁሉ ቀርቦ ካበቃ በኋላ፣ ንጉሡና አብረውት የነበሩት ሁሉ ተንበርክከው ሰገዱ።

30. ንጉሥ ሕዝቅያስና ሹማምቱ፣ ሌዋውያኑ በዳዊትና በባለ ራእዩ በአሳፍ ቃል እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ አዘዙ። እነርሱም ውዳሴውን በደስታ ዘመሩ፤ ራሳቸውንም አጎንብሰው ሰገዱ።

31. ከዚያም ሕዝቅያስ፣ “እነሆ፤ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ቀድሳችኋል፤ አሁንም ቅረቡ፤ መሥዋዕትና የምስጋና ስጦታ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ጉባኤው መሥዋዕትና የምስጋና ስጦታ አመጡ፤ ልባቸው የፈቀደ ሁሉም የሚቃጠል መሥዋዕት አመጡ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 29