ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 18:12-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ሚካያን ሊጠራ ሄዶ የነበረውም መልእክተኛ፣ “እነሆ፣ ሌሎቹ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው፣ ንጉሡ ድል እንደሚያደርግ እየተነበዩ ነው፤ ያንተም ቃል እንደቃላቸው ይሁን፤ ንጉሡን ደስ የሚያሰኘውን ተናገር” አለው።

13. ሚካያ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን ብቻ እናገራለሁ” አለ።

14. እዚያ በደረሰም ጊዜ ንጉሡ፣ “ሚካያ ሆይ፤ ሬማት ዘገለዓድን ለመውጋት እንሂድ ወይስ ልቅር?” ሲል ጠየቀው።እርሱም መልሶ፣ “ሂዱና ድል አድርጉ፤ በእጃችሁ አልፈው ይሰጣሉና” አለው።

15. ንጉሡም፣ “ከእውነት በቀር ምንም ነገር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው።

16. ከዚያም ሚካያ “እስራኤል ሁሉ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበታትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘እነዚህ ሰዎች ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱም በሰላም ወደየቤቱ ይመለስ’ ብሎአል” ሲል መለሰ።

17. የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ስለ እኔ ክፉ ብቻ እንጂ፣ ደግ ትንቢት እንደማ ይናገር አልነገርሁህምን?” አለው።

18. ሚካያም በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይም ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።

19. እግዚአብሔርም፣ ‘የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በሬማት ገለዓድ ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት ማን ያሳስተው?’ አለ።“አንዱ አንድ ሐሳብ፣ ሌላውም ሌላ ሐሳብ አቀረበ።

20. በመጨረሻም አንድ መንፈስ ወደ ፊት ወጥቶ፣ በእግዚአብሔር ፊት በመቆም፣ ‘እኔ አሳስተዋለሁ’ አለ።“እግዚአብሔርም፣ ‘እንዴት አድርገህ?’ ሲል ጠየቀው።

21. “እርሱም፣ ‘እሄድና በነቢያቱ ሁሉ አፍ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ።“እግዚአብሔርም፣ ‘እንግዲያውስ ሂደህ አሳስተው፤ ይሳካልሃልም’ አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 18