ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 6:7-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ከዚያም፣ “በል አውጣና ውሰደው” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘርግቶ ወሰደው።

8. በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ ከእስራኤል ጋር ይዋጋ ነበር፤ ከጦር አለቆቹ ጋር ከተመካከረ በኋላም፣ “በዚህ፣ በዚህ ቦታ እሰፍራለሁ” አለ።

9. የእግዚአብሔርም ሰው፣ “ሶርያውያን በዚያ ታች ወርደዋልና በዚያ በኩል እንዳታልፍ ተጠንቀቅ” ሲል ለእስራኤል ንጉሥ ላከበት።

10. ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ የእግዚአብሔር ሰው የነገረውን ቦታ አስቃኘ፤ ኤልሳዕም ንጉሡን እንደዚህ ካሉት ቦታዎች ራሱን እንዲጠብቅ ከአንድ ሁለት ጊዜ በላይ አስጠነቀቀው።

11. ይህም የሶርያን ንጉሥ እጅግ ስላበሳ ጨው፣ የጦር አለቆቹን ጠርቶ፣ “ከመካከላችን ከእስራኤል ንጉሥ ጋር የተወዳጀ እንዳለ ለምን አትነግሩኝም?” ሲል ጠየቃቸው።

12. ከጦር አለቆቹም አንዱ፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ከእኛ በኩል ማንም ሰው የለም፤ ነገር ግን አንተ በእልፍኝህ ሆነህ እንኳ የምትናገረውን አንዲቱም ሳትቀር ለእስራኤል ንጉሥ የሚነግረው በእስራኤል ያለው ነቢዩ ኤልሳዕ ነው” አለው።

13. ንጉሡም፣ “ሰዎች ልኬ እንዳስይዘው፣ የት እንደሚገኝ ፈልጉ” ሲል አዘዘ። ከዚያም፣ “በዶታይን ይገኛል” የሚል ዜና ደረሰው።

14. ስለዚህ ፈረሶችና ሠረገሎች እንዲሁም ብዙ ሰራዊት ወደዚያ ላከ። እነርሱም በሌሊት ደርሰው ከተማዪቱን ከበቡ።

15. የእግዚአብሔር ሰው አገልጋይ በማለዳ ተነሥቶ ወደ ውጭ ሲወጣ፣ በፈረሶችና በሠረገሎች የተጠናከረ ሰራዊት ከተማዪቱን ከቧት ነበር። አገልጋዩም “ጌታዬ ሆይ፤ ምን ማድረግ ይሻለናል?” ሲል ጠየቀ።

16. ነቢዩም፣ “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ” አለው።

17. ኤልሳዕም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ያይ ዘንድ እባክህ ዐይኖቹን ክፈትለት” ብሎ ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የአገልጋዩን ዐይኖች ከፈተለት፤ ሲመለከትም፤ የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራውን ሞልተውት አየ።

18. ሶርያውያንም ወርደው ወደ እርሱ ሲመጡ ኤልሳዕ፣ “ይህን ሕዝብ ዕውር አድርገው” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ስለዚህ ኤልሳዕ በጠየቀው መሠረት እግዚአብሔር ዕውር አደረጋቸው።

19. ኤልሳዕም፣ “መንገዱ በዚህ አይደለም፤ ከተማዪቱም ይህች አይደለችም፤ ወደምት ፈልጉት ሰው መርቼ እንዳደርሳችሁም እኔን ተከተሉኝ” አላቸው። ከዚያም መርቶ ወደ ሰማርያ ወሰዳቸው።

20. ወደ ከተማዪቱም ከገቡ በኋላ ኤልሳዕ፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲያዩ የእነዚህን ሰዎች ዐይን ክፈት” አለ። እግዚአብሔርም ዐይኖቻቸውን ከፈተ። እነርሱም በሰማርያ ውስጥ መሆናቸውን አዩ።

21. የእስራኤልም ንጉሥ ባያቸው ጊዜ፣ “አባቴ ሆይ፤ ልግደላቸውን? ልፍጃቸውን?” ብሎ ኤልሳዕን ጠየቀው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 6