ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 4:30-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

30. የልጁ እናት ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፤ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፣ ፈጽሞ ትቼህ አልሄድም” አለችው፤ ስለዚህ ተነሥቶ ተከተላት።

31. ግያዝም ቀድሞአቸው ሄዶ በትሩን በልጁ ፊት ላይ አደረገ፤ ነገር ግን ድምፅም፣ ምላሽም አልነበረም። ስለዚህ ግያዝ ወደ ኤልሳዕ ተመልሶ፣ “ልጁ አልነቃም” አለው።

32. ኤልሳዕ ወደ ቤት ሲገባም ልጁ ሞቶ በዐልጋው ላይ ተጋድሞ ነበር።

33. ወደ ውስጥም ገባ፤ ከዚያም በሩን በራሱና በልጁ ላይ ዘግቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።

34. በዐልጋው ላይ ወጥቶም በልጁ ላይ ተጋደመና አፉን በአፉ፣ ዐይኑን በዐይኑ፣ እጁን በእጁ ላይ አደረገ። ሙሉ በሙሉ እንደተ ዘረጋበትም፣ የልጁ ሰውነት መሞቅ ጀመረ።

35. ኤልሳዕም ተነሥቶ በቤቱ ውስጥ ወዲያና ወዲህ ከሄደ በኋላ ወደ ዐልጋው ወጥቶ እንደ ገና በልጁ ላይ ሙሉ ለሙሉ ተዘረጋበት፤ ልጁም ሰባት ጊዜ አስነጠሰውና ዐይኖቹን ከፈተ።

36. ኤልሳዕም ግያዝን ጠርቶ፣ “ሱነማዪቱን ጥራት፤” አለው፤ እርሱም ጠራት። እንደ መጣችም፣ “በይ ልጅሽን ውሰጂ” አላት።

37. እርሷም ገብታ በእግሩ ላይ ወደቀች፤ በምድርም ላይ ተደፋች፤ ልጇንም ይዛ ወጣች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 4