ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 3:15-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. አሁንም ባለ በገና አምጡልኝ።”ታዲያ ባለ በገናው በሚደረድርበት ጊዜ፣ የእግዚአብሔር እጅ በኤልሳዕ ላይ መጣ፤

16. እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር የሚለው እንዲህ ነው፤ ‘በዚህ ሸለቆ ብዙ ጒድጓዶች ቈፍሩ።

17. እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘ነፋስም ሆነ ዝናብ አታዩም፤ ሸለቆው ግን በውሃ ይሞላል፤ እናንተ፣ የቀንድ ከብቶቻችሁና ሌሎች እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ።

18. ይህ በእግዚአብሔር ፊት ቀላል ነገር ነው። ሞዓብንም በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋል።

19. የተመሸጉትን ከተሞችና ያማሩትን ከተሞቻቸውን ሁሉ ድል ታደርጋላችሁ። ውብ ዛፎቻቸውን ሁሉ ትቈርጣላችሁ፤ ምንጮቻቸውን በሙሉ ትደፍናላችሁ፤ መልካሙንም ዕርሻ በድንጋይ ታበላሹታላችሁ።”

20. በማግስቱ መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ፣ እነሆ፤ ከኤዶም በኩል ውሃ እየጐረፈ መጣ፤ ምድሪቱም ውሃ በውሃ ሆነች።

21. በዚህ ጊዜ ነገሥታቱ ሊወጓቸው መምጣታቸውን ሞዓባውያን ሁሉ ሰምተው ነበርና፣ ልጅም ሆነ ሽማግሌ፣ መሣሪያ መያዝ የቻለ ሁሉ ተጠርቶ በመውጣት በጠረፉ ላይ ይጠባበቅ ጀመር።

22. በማግስቱ ጠዋት ማልደው ሲነሡም፣ ፀሓይ በውሃው ላይ ታንጸባርቅ ነበር። ማዶ ላሉት ሞዓባውያንም፣ ውሃው እንደ ደም ቀልቶ ታያቸው።

23. ስለዚህ፣ “ያ እኮ ደም ነው! ያለ ጥርጥር ነገሥታቱ እርስ በርስ ተዋግተው ተራርደዋል። እንግዲህ ሞዓብ ወደ ምርኮህ ዙር!” ተባባሉ።

24. ሞዓባውያን ወደ እስራኤል ሰፈር ሲወጡም፣ እስራኤላውያን ተነሥተው ወጓቸው፤ ሞዓባውያንም ከፊታቸው ሸሹ። ከዚያም እስራኤላውያን ምድሪቱን ወረው ሞዓባውያንን ፈጇቸው።

25. ከተሞቹን ደመሰሱ፤ መልካሙን የዕርሻ መሬት ሁሉ እስኪሸፍ ነው ድረስ፤ እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ ድንጋይ ጣለበት፤ ምንጮቹን በሙሉ ደፈኑ፤ ጥሩ ጥሩውንም ዛፍ ሁሉ ቈርጠው ጣሉ። ቂርሐራሴት ብቻ ከነድንጋይዋ ቀርታ ነበር፤ እርሷም ቢሆን ባለ ወንጭፉ ሰራዊት ከቦ አደጋ ጣለባት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 3