ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 25:15-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. የክብር ዘቡ አዛዥም ከንጹሕ ወርቅና ብር የተሠሩትን ጽናዎችና የመርጫ ወጭቶችን ወሰደ።

16. ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገልገያ ብሎ ከናስ ያሠራቸው ሁለት ዐምዶች፣ የውሃ ማጠራቀሚያው ክብ በርሜልና ተንቀሳቃሽ የዕቃ ማስቀመጫዎቹ ክብደታቸው ከሚዛን በላይ ነበር።

17. እያንዳንዱ ዐምድ ዐሥራ ስምንት ክንድ ሲሆን፣ የናስ ጒልላት ነበረው፤ የጒልላቱ ርዝመት ሦስት ክንድ ሆኖ፣ ዙሪያውን በሙሉ የናስ መርበብና የሮማን ፍሬዎች ቅርጽ ነበረው፤ ሌላውም ዐምድ ከነቅርጾቹ ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ ነበር።

18. የክብር ዘብ አዛዡም ሊቀ ካህኑን ሠራያን፣ በማዕረግ ከእርሱ ቀጥሎ ያለውን ካህኑን ሶፎንያስንና ሦስቱን የበር ጠባቂዎች እስረኛ አድርጎ ወሰዳቸው።

19. እስከዚያች ጊዜ ድረስ በከተማዪቱ ውስጥ ከቀሩትም የተዋጊዎቹን አለቃና አምስት የንጉሡን አማካሪዎች ወሰዳቸው። ደግሞም የአገሩን ሕዝብ ለውትድርና የሚመለምለውን ዋና የጦር አለቃ የነበረውን ጸሓፊውንና በከተማዪቱ ውስጥ የተገኙትን የጸሓፊውን ሥልሳ ሰዎች ወሰዳቸው።

20. አዛዡ ናቡዘረዳንም እነዚህን ሁሉ ይዞ ልብና ወዳለው ወደ ባቢሎን ንጉሥ አመጣቸው።

21. ንጉሡም ሰዎቹን በሐማት ምድር እዚያው ልብና ውስጥ አስገደላቸው። ይሁዳም ከምድሩ በዚህ ሁኔታ ተማርኮ ሄደ።

22. የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር፣ የሳፋን የልጅ ልጅ የሆነውን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን እዚያው በቀረው በይሁዳ ሕዝብ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው።

23. መላው የሰራዊቱ ጦር አለቆችና ሰዎቻቸው የባቢሎን ንጉሥ፣ አገረ ገዥ አድርጎ ጎዶልያስን መሾሙን ሲሰሙ፣ እርሱ ወዳለበት ወደ ምጽጳ መጡ፤ እነርሱም የናታንያ ልጅ እስማኤል፣ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን፣ የነጦፋዊው የተን ሑሜት ልጅ ሠራያ የማዕካታዊው ልጅ ያእዛንያና ሰዎቻቸው ነበሩ።

24. ጎዶልያስም፣ “የባቢሎናውያንን ሹማምት አትፍሩ፤ እዚሁ አገር ኑሩ፤ የባቢሎንን ንጉሥ አገልግሉ፤ ሁሉም ነገር ይሳካላችኋል” ሲል ይህንኑ በቃለ መሐላ አረጋገጠላቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 25