ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 23:25-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. በሙሴ ሕግ በተጻፈው መሠረት በፍጹም ልቡ፣ በፍጹም ነፍሱ፣ በፍጹም ኀይሉ ወደ እግዚአብሔር የተመለሰ፣ እንደ ኢዮስያስ ያለ ንጉሥ፣ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ ፈጽሞ አልተነሣም።

26. ይህም ሆኖ እንኳ ለቊጣ እንዲነሣሣ ምናሴ ካደረጋቸው ነገሮች ሁሉ የተነሣ፣ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ከነደደው ከአስፈሪው ቊጣው ገና አልበረደም ነበር።

27. ስለዚህ እግዚአብሔር፣ “እስራኤልን እንዳስወገድሁ ሁሉ ይሁዳንም ከፊቴ አስወግዳለሁ የመረጥኋትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና፣ ‘ስሜ በዚያ ይሆናል’ ብዬ የተናገር ሁለትን ይህን ቤተ መቅደስ እተዋለሁ” አለ።

28. በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

29. ኢዮስያስ ንጉሥ በነበረበት ዘመን የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ የአሦርን ንጉሥ ለመርዳት ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ወጥቶ ነበር፤ ንጉሥ ኢዮስያስም ጦርነት ሊገጥመው ወጣ፤ ሆኖም ፈርዖን ኒካዑ ፊት ለፊት ገጥሞት መጊዶ ላይ ገደለው።

30. የኢዮስያስም አገልጋዮች ከመጊዶ ሬሳውን በሠረገላ ወደ ኢየሩሳሌም አምጥተው በገዛ መቃብሩ ቀበሩት። የአገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወሰዱት፤ ቀብተውም በአባቱ እግር አነገሡት።

31. ኢዮአክስ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ ሦስት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ሦስት ወር ገዛ። እናቱ አሚጣል ትባላለች፤ እርሷም የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።

32. አባቶቹ እንዳደረጉ ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 23