ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 23:13-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. እንዲሁም ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ ከርኵሰት ኰረብታ በስተ ደቡብ የነበሩትን የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለሲዶናውያን የርኵሰት አምላክ ለአስታሮት፣ ለሞዓብ ሕዝቦች የርኵሰት አምላክ ለካሞሽ፣ ለአሞን ሕዝቦች የርኵሰት አምላክ ለሞሎክ ያሠራቸውን የኰረብታ ላይ ማምለኪያዎች ንጉሡ አረከሰ።

14. አሁንም ኢዮስያስ ማምለኪያ የድንጋይ ሐውልቶችን ሰባበረ፤ የአሼራን ምስል ዐምዶች ቈራረጠ፤ ስፍራውንም በሙታን ዐጥንት ሞላው።

15. እስራኤልን ባሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም የተሠራውን መሠዊያ፣ በቤቴል የነበረውን ያን የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራ፣ መሠዊያው ያለበትን ያን የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራ እንኳ እንደዚሁ አፈረሰ፤ ድንጋዮቹን ሰባበረ፤ እንደ ዱቄትም አደቀቃቸው፤ የአሼራንም ምስል ዐምድ አቃጠለ።

16. ኢዮስያስ ዘወር ሲል በኰረብታው ላይ የነበሩትን መቃብሮች አየ፤ ዐፅሞቹንም ከየመቃብሩ አስወጣ፤ ያ የእግዚአብሔር ሰው አስቀድሞ እንደ ተናገረው፣ የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ መሠዊያውን ለማርከስ ሲል ዐፅሞቹን በላዩ ላይ አቃጠለበት።

17. ንጉሡም፣ “ያ የማየው የመቃብር ሐውልት የማን ነው?” ሲል ጠየቀ የከተማዪቱም ሰዎች፣ “ከይሁዳ መጥቶ አሁን አንተ ያደረግኸውን ነገር ሁሉ በቤቴል መሠዊያ ላይ እንደሚደርስ የተናገረ የዚያ የእግዚአብሔር ሰው መቃብር ነው” አሉት።

18. ኢዮስያስም፣ “በሉ እንዳለ ተዉት፤ ዐፅሙን ማንም ሰው ከቦታው እንዳያንቀሳ ቅሰው” አለ፤ ስለዚህ የእርሱንና ከሰማርያ የመጣውን ነቢይ ዐፅም ሳይነኩ እንዳለ ተውት።

19. ኢዮስያስም በቤቴል እንዳደረገው ሁሉ በሰማርያም ከተሞች ኰረብቶች ላይ የእስራኤል ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትንና እግዚአብሔርን ያስቈጡበትን ቤተ ጣዖቶች ሁሉ አስወገደ፤ አረከሳቸውም።

20. ኢዮስያስ እነዚያን የየኰረብታውን ማምለኪያ ቦታ ካህናትን ሁሉ፣ በየመሠዊያው ላይ ዐረዳቸው፤ በመሠዊያዎቹ ላይ የሰው ዐፅም አቃጠለ፣ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 23