ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 23:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም ንጉሡ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠራ።

2. የይሁዳን ሰዎች ሁሉ፣ የኢየሩሳሌምን ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ፣ ካህናቱንና ነቢያቱን ሁሉ ከልጅ እስከ ዐዋቂ አንድም ሰው ሳይቀር ይዞአቸው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መጣ። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተገኘውንም የኪዳኑን መጽሐፍ ቃል በጆሮአቸው እንዲሰሙት በሙሉ አነበበላቸው።

3. ንጉሡም በዐምደ ወርቁ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ እግዚአብሔርን እንደሚከተል ትእዛዞቹን፣ ደንቦቹን፣ ሥር ዐቶቹን በፍጹም ልቡ፣ በፍጹምም ነፍሱ እንደሚጠብቅ፣ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን ኪዳን እንደሚያጸና በእግዚአብሔር ፊት ኪዳኑን አደሰ፤ ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ ለኪዳኑ ያላቸውን ታማኝነት አረጋገጡ።

4. ንጉሡም ለበኣል፣ ለአሼራና ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊት ሁሉ የተሠሩትን የመገልገያ ዕቃዎች በሙሉ፣ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲያወጡ ሊቀ ካህናቱን ኬልቅያስን በሁለተኛ ማዕረግ ያሉትን ካህናትና የቤተ መቅደሱን በር ጠባቂዎች አዘዘ። ዕቃዎቹንም ከኢየሩሳሌም ውጭ በቄድሮን ሸለቆ ሜዳ ላይ አቃጠላቸው፤ ዐመዱንም ወደ ቤቴል ወሰደው።

5. በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ዙሪያ በሚገኙ ኰረብቶች ላይ ዕጣን እንዲያጥኑ የይሁዳ ነገሥታት የሾሙአቸውን የጣዖት ካህናት አባረረ እንዲሁም ለበኣል፣ ለፀሓይና ለጨረቃ፣ ለስብስብ ከዋክብትና ለመላው የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት የሚያጥኑትን አስወገደ።

6. የአሼራንም ምስል ዐምድ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አውጥቶ ከኢየሩሳሌም ውጭ ወዳለው ወደ ቄድሮን ሸለቆ ወስዶ አቃጠለው፤ አድቅቆ ፈጭቶም በሕዝቡ መቃብር ላይ በተነው።

7. እንዲሁም ስለ አምልኮ ባዕድ ሥርዐት በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የቤተ ጣዖት ወንደቃዎችን ክፍሎችና ሴቶች ለአሼራ መጋረጃ የሚፈትሉባቸውን ክፍሎች አፈረሰ።

8. ኢዮስያስ የቤተ ጣዖት ካህናትን ሁሉ ከይሁዳ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም አወጣቸው፤ ከጌባ ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ፣ ካህናቱ ዕጣን ያጥኑባቸው የነበሩትን የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራዎችን አረከሰ። ከከተማዪቱ በር በስተ ግራ በኩል፣ በከተማዪቱ ገዥ በኢያሱ በር መግቢያ አጠገብ የነበሩትን የበሮቹን ማምለኪያ ስፍራዎች አፈረሰ።

9. የየኰረብታው ማምለኪያ ካህናት ኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ባያገለግሉም እንኳ ከካህናት ወንድሞቻቸው ጋር እርሾ ያልነካው ቂጣ ይበሉ ነበር።

10. በሄኖም ሸለቆ የነበረውን ቶፌት የተባለውን ማምለኪያ አረከሰ፤ ይኸውም ማንም ሰው ወንድ ወይም ሴት ልጁን ለሞሎክ በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ እንዳያቀርብበት ነው።

11. የይሁዳ ነገሥታት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግቢያ ላይ ለፀሓይ አምልኮ የሰጡአቸውን ፈረሶች ከዚያ አስወገደ። እነዚህም ናታን ሜሌክ በተባለ በአንድ ሹም ቤት አጠገብ በአደባባዩ ላይ ነበሩ። ኢዮስያስም ለፀሐይ አምልኮ የተሰጡትን ሠረገሎች አቃጠለ።

12. የይሁዳ ነገሥታት በላይኛው የአካዝ እልፍኝ አጠገብ በሰገነቱ ላይ ያቆሟቸውን መሠዊያዎች፣ ምናሴም በሁለቱ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች ላይ ያሠራቸውን መሠዊያዎች አስወገደ፤ ስብርብራቸውን አወጣ፤ ድቃቂውንም አንሥቶ ወደ ቄድሮን ሸለቆ ጣለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 23