ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 22:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኢዮስያስ ሲነግሥ ዕድሜው ገና ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም የባሱሮት አገር ሰው የአዳያ ልጅ ይዲዳ ነበረች።

2. ኢዮስያስም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም፤ አባቱ ዳዊት በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ።

3. በዘመነ መንግሥቱ በዐሥራ ስምንተኛውም ዓመት ኢዮስያስ የሜሶላምን የልጅ ልጅ የኤዜልያስን ልጅ ጸሓፊውን ሳፋንን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ላከው፤ እንዲህም አለው፤

4. “ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ኬልቅያስ ውጣ፤ የበር ጠባቂዎች ከሕዝቡ ሰብስበው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ ራሱ እንዲቈጥረው አድርግ፤

5. ይህም የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲቈጣጠሩ ለተሾሙት ሰዎች ይሰጥ፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለሚያድሱት ይክፈሏቸው፤

6. የሚከፍሉትም ለአናጺዎች፣ ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ነው። እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሥራ የሚሆኑ ሳንቃዎችና የተጠረቡ ድንጋዮች ይግዙበት።

7. ሰዎቹ ታማኞች ስለ ሆኑም የተሰጣቸውን ገንዘብ መቈጣጠር አያስፈልግም።”

8. ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ ጸሓፊውን ሳፋንን፣ “የሕጉን መጽሐፍ እኮ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አገኘሁት” ብሎ ሰጠው፤ እርሱም ተቀብሎ አነበበው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 22