ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 19:19-34 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. አሁንም እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ እግዚአብሔር አንተ ብቻ አምላክ መሆንህን እንዲያውቁ፣ ከእጁ አድነን።”

20. ከዚያም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ ሕዝቅያስ እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘በአሦር ንጉሥ በሰናክሬም ላይ ወደ እኔ ያቀረብኸውን ልመና ሰምቻለሁ።

21. እንግዲህ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤“ ‘ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ፣ትንቅሃለች፤ ታቃልልሃለችም፤የኢየሩሳሌም ልጅ፣አንተ በላይዋ ስትበር ራሷን ትነቀንቅብሃለች።

22. ለመሆኑ የሰደብኸውና ያቃለልኸው ማንን ነው?ድምፅህንስ ከፍ ያደረግኸው?ዐይንህንስ በኵራት ያነሣኸው በማን ላይ ነው?በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው እንዴ?

23. በመልእክተኞችህ አማካይነት፣በአምላክ ላይ የስድብ መዓት አውርደሃል፤እንዲህም ብለሃል፤“በብዙ ሠረገሎቼ፣የተራሮቹን ከፍታ፣የሊባኖስንም የመጨረሻ ጫፍ ወጥቻለሁ፤ረጃጅም ዝግባዎቹን፣ምርጥ የሆኑ ጥዶቹንም ቈርጫለሁ፤ወደ ሩቅ ዳርቻዎቹ፣ወደ ውብ ደኖቹም ደርሻለሁ።”

24. “በሌሎች አገሮችም የውሃ ጒድጓዶች ቈፍሬአለሁ፤በዚያም ውሃ ጠጥቻለሁ፤በእግሬ ጫማዎችም፣የግብፅን ምንጮች ሁሉ ረግጬ አድርቄአለሁ።”

25. “ ‘ከብዙ ጊዜ በፊት፣ይህን እኔ እንዳደረግሁት አልሰማህም ነበርን?ዕቅዱን ገና ድሮ አውጥቼ፣አሁን ግን እንዲፈጸም አደረግሁት፤ይህም የተመሸጉትን ከተሞች፣አንተ የድንጋይ ክምር ማድረግህ ነው።

26. የሚኖሩባቸውም ሰዎች ኀይላቸው ተሟጦ አልቆአል፤ደንግጠውም የኀፍረት ማቅ ለብሰዋል፤ሜዳ ላይ እንደ በቀለ ተክል፣ገና እንዳልጠነከረ የቡቃያ ሥር፣በቤት ጣራ ላይ በቅሎ፣ገና ሳያድግ እንደ ጠወለገ ሣርም ሆነዋል።

27. “ ‘የት እንደምትቀመጥ፣መቼ መጥተህ መቼ እንደምትሄድ፣በእኔም ላይ የተቈጣኸውን ቊጣ ዐውቃለሁ።

28. በእኔ ላይ በመቈጣትህ፣ንቀትህም ወደ ጆሮዬ ስለ ደረሰ፣ስናጋዬን በአፍንጫህ አደርጋለሁ፤ልጓሜን በአፍህ አገባለሁ፤በመጣህበትም መንገድእንድትመለስ አደርጋለሁ።’

29. “ሕዝቅያስ ሆይ፤ ምልክቱ ይህ ነው፤“በዚህ ዓመት በገዛ እጁ የበቀለውን፣በሚመጣው ዓመት ደግሞ የገቦውን እህል ትበላላችሁ፤በሦስተኛው ዓመት ግን ትዘራላችሁ፤ ታጭዳላችሁ፤ወይንም ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ።

30. አሁንም ከዳዊት ቤት የተረፉት፣ሥራቸውን ወደ ታች ይሰዳሉ፤ ወደ ላይም ፍሬ ያፈራሉ።

31. ከኢየሩሳሌም በሕይወት የተረፉት፣ከጽዮን ተራራም ከሞት ያመለጡት ይወጣሉና። የእግዚአብሔር ቅናት ይህን ታደርጋለች።

32. “እንግዲህ እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፤“ወደዚች ከተማ ፈጽሞ አይገባም፤አንዲትም ፍላጻ አይወረውርባትም፤ጋሻ አንግቦ ወደ እርሷ አይቀርብም፤በዐፈርም ቊልል አይከባትም።

33. በመጣበት መንገድ ተመልሶ ይሄዳል፤ተመልሶ ይሄዳታል እንጂ ወደዚች ከተማ ፈጽሞ አይገባም፤ይላል እግዚአብሔር።

34. ስለ ራሴና ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ስል፣ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 19