ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 19:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. “ሂዱና ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት፤ ‘የምትመካበት አምላክ፣ “ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትወድቅም” በማለት እንዳያታልልህ።

11. መቼም የአሦር ነገሥታት በአገሮች ሁሉ ላይ ምን እንዳደረጉ ሰምተሃል፤ ፈጽሞ አጥፍተዋቸዋል፤ ታዲያ አንተስ ከዚህ የምታመልጥ ይመስልሃልን?

12. የቀድሞ አባቶቼ ያጠፏቸውን ሕዝቦች ማለትም ጎዛንን፣ ካራንን፣ ራፊስን እንዲሁም በተላሳር የነበሩትን የዔድንን ሰዎች አማልክታቸው አድነዋቸዋልን?

13. ለመሆኑ የሐማትና የአርፋድ ነገሥታት የት አሉ? የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥስ የት አለ? ደግሞስ የሄና ወይም የዒዋ ነገሥታት የት አሉ?

14. ሕዝቅያስም ደብዳቤውን ከመልእክተኞቹ ተቀብሎ አነበበው፤ ከዚያም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጥቶ ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው።

15. ከዚያም ሕዝቅያስ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ “በኪሩቤል ላይ በዙፋንህ የተቀመጥህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር ነገሥታት ሁሉ ላይ አምላክ አንተ ብቻ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን የፈጠርህም አንተ ነህ።

16. እግዚአብሔር ሆይ፤ አሁንም ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐይንህንም ክፈትና እይ፤ ሰናክሬም ሕያው እግዚአብሔርን ይሰድብ ዘንድ የላከውንም ቃል አድምጥ።

17. “እግዚአብሔር ሆይ፤ የአሦር ነገሥታት እነዚህን አሕዛብንና ምድራቸውን በርግጥ አጥፍተዋል።

18. አማልክቶቻቸውን በእሳት ውስጥ ጥለው አቃጥለዋቸዋል፤ በሰው እጅ የተሠሩ ዕንጨትና ደንጊያ ብቻ እንጂ አማልክት አልነበሩምና።

19. አሁንም እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ እግዚአብሔር አንተ ብቻ አምላክ መሆንህን እንዲያውቁ፣ ከእጁ አድነን።”

20. ከዚያም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ ሕዝቅያስ እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘በአሦር ንጉሥ በሰናክሬም ላይ ወደ እኔ ያቀረብኸውን ልመና ሰምቻለሁ።

21. እንግዲህ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤“ ‘ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ፣ትንቅሃለች፤ ታቃልልሃለችም፤የኢየሩሳሌም ልጅ፣አንተ በላይዋ ስትበር ራሷን ትነቀንቅብሃለች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 19