ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 16:5-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ለመውጋትና አካዝን ለመክበብ ወጡ፤ ይሁን እንጂ ሊያሸንፉት አልቻሉም።

6. በዚያን ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ረአሶን የይሁዳን ሰዎች አሳዶ፣ ኤላትን ወደ ሶርያ ግዛት መለሰ፤ ከዚያም ኤዶማውያን ወደ ኤላት መጥተው እስከ ዛሬ በዚያ ይኖራሉ።

7. ከዚህ የተነሣም አካዝ፣ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር፣ “እኔ አገልጋይህም ልጅህም ነኝ፤ ስለዚህ መጥተህ ከሚወጉኝ ከሶርያ ንጉሥና ከእስራኤል ንጉሥ እጅ አድነኝ” ሲል መልእክተኞች ላከበት።

8. አካዝም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች የሚገኘውን ብርና ወርቅ አውጥቶ ለአሦር ንጉሥ ገጸ በረከት ላከለት።

9. የአሦር ንጉሥም፣ የአካዝን ልመና በመቀበል፤ ደማስቆን አጥቅቶ ያዛት፤ ሕዝቧን ማርኮ ወደ ቂር አፈለሳቸው፤ ረአሶንንም ገደለው።

10. ከዚያም ንጉሥ አካዝ የአሦርን ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶርን ለመገናኘት ወደ ደማስቆ ሄደ። በደማስቆም ያለውን መሠዊያ አይቶ፣ ንድፉን ከዝርዝር ጥናቱ ጋር ለካህኑ ለኦርያ ላከለት።

11. ካህኑ ኦርያም ንጉሥ አካዝ ከደማስቆ በላከለት ዝርዝር ጥናት መሠረት መሠዊያ ሠራ፤ ንጉሡ አካዝ ከመመለሱም በፊት አጠናቀቀው።

12. ንጉሡ ከደማስቆ ተመልሶ በመጣ ጊዜ፣ መሠዊያውን አየ፤ ቀርቦም በመሠዊያው ላይ ወጣ፤

13. ከዚያም የሚቃጠል መሥዋዕቱንና የእህል ቊርባኑን በመሠዊያው ላይ አቀረበ፤ የመጠጥ ቊርባኑን አፈሰሰ፤ የኅብረት መሥዋዕቱንም ደም በመሠዊያው ላይ ረጨ።

14. በአዲሱ መሠዊያና በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መካከል፣ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ የነበረውን የናስ መሠዊያ፣ ከቦታው አሥነስቶ ከአዲሱ መሠዊያ በስተ ሰሜን በኩል አኖረው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 16