ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 21:5-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. እነርሱም፣ “እንድንፈራርስና በእስራኤልም ውስጥ በየትኛውም ስፍራ እንዳንኖር ካጠፋንና ደባ ከፈጸመብን ሰው

6. ከእርሱ ዘሮች ሰባት ወንዶች ልጆች ይሰጠን፤ እኛም ከእግዚአብሔር በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ በእግዚአብሔር ፊት እንስቀላቸው” ብለው መለሱለት።ስለዚህ ንጉሡ፣ “እሺ እሰጣችኋለሁ” አለ።

7. ንጉሥ ዳዊት በራሱና በሳኦል ልጅ በዮናታን መካከል በእግዚአብሔር ፊት ስላደረጉት መሐላ ሲል የሳኦልን ልጅ፣ የዮናታንን ልጅ ሜምፊቦስቴን ከሞት አተረፈ።

8. ነገር ግን ንጉሡ የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ለሳኦል የወለደቻቸውን ሁለቱን ወንዶች ልጆች ሄርሞንንና ሜምፊቦስቴን፤ የሳኦል ልጅ ሜሮብ ለምሓላታዊው ለቤርዜሊ ልጅ ለኤስድሪኤል የወለደችለትን አምስት ወንዶች ልጆች ጭምር ወሰደ፤

9. ለገባዖናውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ገድለው በኰረብታው ላይ በእግዚአብሔር ፊት ሰቀሏቸው። ሰባቱም በአንድነት ወደቁ፤ የተገደሉትም በመከሩ ወራት የመጀመሪያ ቀኖች፣ የገብስ ዐጨዳ በተጀመረበት ዕለት ነበር።

10. የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ፣ በቋጥኝ ላይ ለራሷ አነጠፈች፤ ከመከር ወቅት መጀመሪያ አንሥቶ ዝናብ ከሰማይ በሬሳዎቹ ላይ እስከ ወረደ ጊዜ ድረስ ቀን የሰማይ ወፎች ሌሊት የዱር አራዊት እንዲነኳቸው አልፈቀደችም፤

11. የሳኦል ቁባት የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ዳዊት በሰማ ጊዜ፣

12. ሄዶ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ወሰደ፤ የኢያቢስ ሰዎች፣ ፍልስጥኤማውያን ሳኦልን በጊልቦዓ ከገደሉ በኋላ እነርሱን ከሰቀሉት ከቤትሳን አደባባይ በድብቅ ወስደዋቸው ነበር።

13. ዳዊትም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከዚያ አመጣ፤ እንዲሁም የእነዚያን የተገደሉትን ሰዎች ዐፅም ሰበሰቡ።

14. የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም በብንያም አገር ጼላ በተባለ ስፍራ በሳኦል አባት በቂስ መቃብር ቀበሩት፤ ንጉሡ ያዘዘውንም ሁሉ አደረጉ። ከዚያ በኋላም ስለ ምድሪቱ የቀረበውን ጸሎት እግዚአብሔር ሰማ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 21