ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 16:10-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ንጉሡ ግን፣ “እናንት የጽሩያ ልጆች እናንተንና እኔን የሚያገናኘን ምን ነገር አለ? እግዚአብሔር፣ ‘ዳዊትን ርገመው’ ብሎት የሚረግመኝ ከሆነ፣ ‘ይህን ለምን አደረግህ’ ብሎ ማን ሊጠይቀው ይችላል?” አለው።

11. ከዚያም ዳዊት አቢሳንና ሹማምቱን ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “ከአብራኬ የወጣው ልጄ ሕይወቴን ሊያጠፋት ከፈለገ፣ ይህ ብንያማዊ ቢያደርገው ምን ያስደንቃል? ስለዚህ ተዉት፤ እግዚአብሔር በል ብሎት ነውና ይራገም፤

12. ምናልባትም እግዚአብሔር ሐዘኔን አይቶ በዛሬውም ርግማን ፈንታ በጎ ነገር ያደርግልኝ ይሆናል።”

13. ስለዚህም ዳዊትና ሰዎቹ መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ሳሚም በአንጻሩ ባለው ኰረብታ ጥግ ጥግ እየሄደ ይራገም፣ ድንጋይ ይወረውርበትና ዐፈር ይበትንበት ነበር።

14. ንጉሡና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ ለመሄድ ወዳሰቡበት ስፍራ ደረሱ፤ በጣም ደክሞአቸው ስለ ነበር በዚያ ዐረፉ።

15. በዚህን ጊዜ አቤሴሎምና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ አኪጦፌልም አብሮት ነበር።

16. የዳዊት ወዳጅ አርካዊው ኩሲም ወደ አቤሴሎም መጥቶ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፤ ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ” አለው።

17. አቤሴሎምም፣ ኩሲን፣ “ለወዳጅህ ያለህ ታማኝነት እስከዚህ ድረስ ነው? ለምን ከወዳጅህ ጋር አልሄድህም?” ሲል ጠየቀው።

18. ኩሲም፣ አቤሴሎምን እንዲህ አለው፤ “ይህንንስ አላዳርገውም! እኔ በእግዚአብሔር፣ በዚህ ሕዝብና በእስራኤል ሰዎች ሁሉ ለተመረጠው ለእርሱ እሆናለሁ፤ አብሬውም እኖራለሁ፤

19. እንግዲህ ልጁን ካላገለገልሁ ማንን ላገለግል ነው? አባትህን እንዳገለገልሁ ሁሉ፤ አንተንም አገለግላለሁ።”

20. አቤሴሎምም አኪጦፌልን፤ “እስቲ ምክር አምጣ፤ ምን እናድርግ?” አለው።

21. አኪጦፌልም መልሶ፣ “ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁ አባትህ ከተዋቸው ቁባቶቹ ጋር ግባና ተኛ፤ ከዚያም አንተ፣ አባትህን እጅግ የጠላህ መሆንህን መላው እስራኤል ይሰማና አብሮህ ያለው ሁሉ ክንዱ ይበረታል” አለው።

22. ስለዚህ ለአቤሴሎም በሰገነቱ ላይ ድንኳን ተከሉለት፤ እዚያም መላው እስራኤል እያየው ከአባቱ ቁባቶች ጋር ተኛ።

23. በዚያም ጊዜ አኪጦፌል የሚሰጠው ምክር ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ መጠየቅ ይቈጠር ነበር፤ ዳዊትም ሆነ አቤሴሎም የአኪጦፌልን ምክር የሚቀበሉት በዚህ ሁኔታ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 16