ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 11:2-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. አንድ ቀን ማታ፣ ዳዊት ከዐልጋው ተነሥቶ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር፤ ከሰገነቱ ላይ እንዳለም፣ አንዲት ሴት ገላዋን ስትታጠብ አየ፤ ሴቲቱም እጅግ በጣም ውብ ነበረች።

3. ዳዊትም ሰው ልኮ ስለ ሴቲቱ አጠያየቀ። ሰውየውም፣ “ይህች የኤልያብ ልጅ፣ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ አይደለችምን?” አለ።

4. ከዚያም ዳዊት መልእክተኞች ልኮ አስመጣት፤ እርሱ ወዳለበት ገባች፤ አብሮአትም ተኛ። በዚህም ጊዜ ወርሐዊ የመንጻት ጊዜዋን ፈጽማ ነበር። ከዚያም ተመልሳ ወደ ቤቷ ሄደች።

5. ሴቲቱ ፀነሰች፤ ለዳዊትም፣ “አርግዣለሁ” ብላ ላከችበት።

6. ስለዚህም ዳዊት ለኢዮአብ፣ “ኬጢያዊውን ኦርዮን ወደ እኔ ስደደው” ሲል ላከበት፤ ኢዮአብም ወደ ዳዊት ላከው።

7. ኦርዮን በመጣ ጊዜም፣ ዳዊት የኢዮአብንና የሰራዊቱን ሁሉ ደኅንነት እንዲሁም ጦርነቱ እንዴት እየተካሄደ እንዳለ ጠየቀው።

8. ከዚያም ዳዊት ኦርዮን፣ “በል እንግዲህ ወደ ቤትህ ወርደህ እግርህን ታጠብ” አለው። ኦርዮን ከቤተ መንግሥት ተሰናብቶ ወጣ፤ ንጉሡም ማለፊያ ምግብ አስከትሎ ላከለት።

9. ነገር ግን ኦርዮ ከጌታው አገልጋዮች ሁሉ ጋር በቤተ መንግሥቱ ቅጽር በር ተኛ እንጂ፣ ወደ ቤቱ አልወረደም ነበር።

10. ዳዊት፣ “ኦርዮን ወደ ቤቱ አልሄደም” መባሉን ሲሰማ ኦርዮን፣ “ከመንገድ ገና አሁን መግባትህ አይደለምን? ወደ ቤትህ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 11