ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 1:4-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ዳዊትም፣ “ምን ነገር ተፈጠረ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም “ሰዎቹ ከጦርነቱ ሸሽተዋል፤ ብዙዎቹ ወድቀዋል፤ ሞተዋል፤ ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ሞተዋል” አለ።

5. ከዚያም ዳዊት ወሬውን የነገረውን ወጣት፣ “ሳኦልና ልጁ ዮናታን መሞታቸውን እንዴት አወቅህ?” ሲል ጠየቀው።

6. ወሬ ነጋሪው ወጣትም እንዲህ አለ፤ “ድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ ወጥቼ ነበር፤ እዚያም ሳኦል ጦሩን ተደግፎ ሳለ፣ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ተከታትለው ደረሱበት፤

7. ወደ ኋላውም ዞር ሲል እኔን ስላየ ጠራኝ፤ እኔም፣ ‘ምን ልታዘዝ’ አልሁ።

8. “እርሱም፣ ‘አንተ ማን ነህ?’ ሲል ጠየቀኝ፤“እኔም ‘አማሌቃዊ ነኝ’ ብዬ መለስሁለት።

9. “ከዚያም፣ ‘እኔ በሞት ጣር ውስጥ እገኛለሁ፤ ነፍሴ ግን አልወጣችም፤ እባክህ በላዬ ቆመህ ግደለኝ’ አለኝ።

10. “መቼም ከወደቀ በኋላ እንደማይተርፍ ስላወቅሁ፣ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱ ላይ የነበረውን ዘውድና የክንዱን አንባር ወስጄ እነሆ፤ ለጌታዬ አምጥቻለሁ።”

11. ከዚያም ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ ልብሳቸውን ቀደዱ።

12. ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን፣ ለእግዚአብሔር ሰራዊትና ለእስራኤል ቤት አዘኑ፤ አለቀሱ፤ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ፤ የወደቁት በሰይፍ ነበርና።

13. ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ወጣት፣ “ከየት ነው የመጣኸው?” ብሎ ጠየቀው።እርሱም፣ “እኔ የአንድ መጻተኛ አማሌቃዊ ልጅ ነኝ” ብሎ መለሰ።

14. ዳዊትም፣ “ታዲያ እግዚአብሔር የቀባውን ለማጥፋት እጅህን ስታነሣ እንዴት አልፈራህም?” ሲል ጠየቀው።

15. ዳዊትም ከጒልማሶቹ አንዱን ጠርቶ፣ “በል ቅረብና ውደቅበት” አለው። እርሱም መታው፤ ሞተም።

16. ዳዊትም፣ “እግዚአብሔር የቀባውን ገድያለሁ’ ስትል የገዛ አፍህ መስክሮብሃልና፣ ደምህ በራስህ ላይ ይሁን” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 1