ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 1:14-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ዳዊትም፣ “ታዲያ እግዚአብሔር የቀባውን ለማጥፋት እጅህን ስታነሣ እንዴት አልፈራህም?” ሲል ጠየቀው።

15. ዳዊትም ከጒልማሶቹ አንዱን ጠርቶ፣ “በል ቅረብና ውደቅበት” አለው። እርሱም መታው፤ ሞተም።

16. ዳዊትም፣ “እግዚአብሔር የቀባውን ገድያለሁ’ ስትል የገዛ አፍህ መስክሮብሃልና፣ ደምህ በራስህ ላይ ይሁን” አለው።

17. ዳዊትም በሳኦልና በልጁ በዮናታን ሞት ምክንያት ይህን የሐዘን እንጒርጒሮ እየተቀኘ አለቀሰ፤

18. እንዲሁም የቀስት እንጒርጒሮ የተባለውን ለይሁዳ ሕዝብ እንዲያስተምሩ አዘዘ፤ ይህም በያሻር መጽሐፍ ተጽፎአል።

19. “እስራኤል ሆይ፤ ክብርህ በኰረብቶችህ ላይ ተወግቶ ሞቶአል፤ኀያላኑ እንዴት እንደዚህ ይውደቁ!

20. “ይህን በጌት አትናገሩ፤በአስቀሎናም መንገዶች አታውጁት፤የፍልስጥኤም ቈነጃጅት አይደሰቱ፤ያልተገረዙት ሴቶች ልጆች እልል አይበሉ።

21. “እናንተ የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ፤ጠል አያረስርሳችሁ፤ዝናብም አይውረድባችሁ፤የቍርባን እህል የሚያበቅሉም ዕርሻዎች አይኑራቸው፤በዚያ የኀያሉ ሰው ጋሻ ረክሶአልና፤ የሳኦል ጋሻ ከእንግዲህ በዘይት አይወለወልም።

22. ከሞቱት ሰዎች ደም፣ከኀያላኑም ሥብ፣የዮናታን ቀስት ተመልሳ አልመጣችም፤የሳኦልም ሰይፍ በከንቱ አልተመለሰችም።

23. “ሳኦልና ዮናታን በሕይወት እያሉ፣የሚዋደዱና የሚስማሙ ነበሩ፤ሲሞቱም አልተለያዩም፤ከንስርም ይልቅ ፈጣኖች፣ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ።

24. “እናንት የእስራኤል ቈነጃጅት ሆይ፤ሐምራዊ ቀሚስና ቀጭን ፈትል ላለበሳችሁ፣ልብሶቻችሁንም በወርቀ ዘቦ ላስጌጠላችሁ፣ለሳኦል አልቅሱለት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 1