ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 21:12-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. የሦስት ዓመት ራብ ወይስ የጠላቶችህ ሰይፍ ለሦስት ወር አይሎብህ መጥፋት ወይስ ሦስት ቀን የእግዚአብሔር ሰይፍ መቅሠፍት በምድሪቱ ላይ ወርዶ የእግዚአብሔር መልአክ እስራኤልን ሁሉ ያጥፋ?’ ለላከኝ ምን እንደምመልስ ቍርጡን ንገረኝ።”

13. ዳዊትም ጋድን፣ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ መሕረቱ ታላቅ ስለ ሆነ በእግዚአብሔር እጅ መውደቅ ይሻለኛል፤ በሰው እጅስ አልውደቅ” አለ።

14. ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ መቅሠፍት ላከ፤ ከእስራኤልም ሰባ ሺህ ሰው ዐለቀ።

15. እንዲሁም እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፉ መልአክ ላከ፤ መልአኩ ሊያጠፋትም ሲል እግዚአብሔር አይቶ ስለሚደርሰው ጥፋት አዘነ፤ ሕዝቡን የሚያጠፋውንም መልአክ፣ “እጅህን መልስ” አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር።

16. ዳዊት ቀና ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔር መልአክ በሰማይና በምድር መካከል ቆሞ አየ፤ መልአኩም በኢየሩሳሌም ላይ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ ይዞ ነበር፤ ከዚያም ዳዊትና ሽማግሌዎቹ ማቅ እንደ ለበሱ በግምባራቸው ተደፉ።

17. ዳዊት እግዚአብሔርን፣ “ተዋጊዎቹ እንዲቈጠሩ ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? ኀጢአት የሠራሁትም ሆነ የበደልሁት እኔ ነኝ፤ እነዚህ እኮ በጎች ናቸው፤ ታዲያ እነርሱ ምን አደረጉ? እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን እንጂ፣ መቅሠፍቱ በሕዝብህ ላይ አይውረድ” አለ።

18. ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራ ዘንድ እንዲነግረው ጋድን አዘዘው።

19. ዳዊትም ጋድ በእግዚአብሔር ስም በነገረው ቃል መሠረት ለመፈጸም ወጣ።

20. ኦርና ስንዴ በመውቃት ላይ ሳለ ዘወር ሲል መልአኩን አየ፤ አብረውት የነበሩት አራት ወንዶች ልጆቹም ተሸሸጉ።

21. ዳዊት ወደ እርሱ እየቀረበ መጣ፤ ኦርና ቀና ብሎ ሲመለከት፣ ዳዊትን አየው፤ ከዐውድማውም ወጥቶ መሬት ላይ ለጥ ብሎ በመደፋት ለዳዊት እጅ ነሣ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 21