ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27
  28. 28
  29. 29

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዳዊት ተዋጊ ሰራዊቱን ቈጠረ

1. ሰይጣን በእስራኤል ላይ ተነሥቶ ዳዊት የእስራኤልን ሕዝብ እንዲቈጥር አነሣሣው።

2. ዳዊትም ኢዮአብንና የሰራዊቱን አዛዦች፣ “ሄዳችሁ ከቤርሳቤህ እስከ ዳን ያሉትን እስራኤላውያን ቍጠሩ፤ ከዚያም ምን ያህል እንደሆኑ አውቅ ዘንድ ንገሩኝ” አላቸው።

3. ኢዮአብ ግን፣ “እግዚአብሔር የእስራኤልን ሰራዊት አሁን ካለው በላይ በመቶ እጥፍ ያብዛው፤ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ ሁሉስ ቢሆኑ የጌታዬ ተገዢዎች አይደሉምን? ታዲያ ጌታዬ ይህን ማድረግ ለምን አስፈለገው? ለምንስ በእስራኤል ላይ በደል ያመጣል?” አለ።

4. ይሁን እንጂ የንጉሡ ቃል ኢዮአብን አሸነፈው፤ ስለዚህ ኢዮአብ ወጣ፤ በመላው እስራኤል ከተዘዋወረ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።

5. ኢዮአብም የተዋጊዎቹን ሰዎች ቍጥር ለዳዊት አቀረበ፤ እነዚህም በመላው እስራኤል አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ፣ በይሁዳ ደግሞ አራት መቶ ሰባ ሺህ ሲሆኑ፣ ሁሉም ሰይፍ መምዘዝ የሚችሉ ነበሩ።

6. ኢዮአብ ግን የንጉሡ ትእዛዝ አስጸያፊ ነበረና፣ የሌዊንና የብንያምን ነገድ ጨምሮ አልቈጠረም።

7. ይህ ትእዛዝ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እስራኤልን ቀጣ።

8. ከዚያም ዳዊት እግዚአብሔርን፣ “ይህን በማድረጌ እጅግ በድያለሁ፤ የፈጸምሁትም የስንፍና ሥራ ስለ ሆነ፣ የባሪያህን በደል እንድታስወግድ እለምንሃለሁ” አለ።

9. እግዚአብሔርም የዳዊት ባለ ራእይ የሆነውን ጋድን እንዲህ አለው፤

10. “ሂድና ለዳዊት እንዲህ ብለው ንገረው፤ ‘እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ እነሆ፣ ሦስት ምርጫ ሰጥቼሃለሁ፤ በአንተ ላይ እንዳደርስብህ አንዱን ምረጥ።’ ”

11. ስለዚህ ጋድ ወደ ዳዊት ሄዶ እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘በል እንግዲህ አንዱን ምረጥ፤

12. የሦስት ዓመት ራብ ወይስ የጠላቶችህ ሰይፍ ለሦስት ወር አይሎብህ መጥፋት ወይስ ሦስት ቀን የእግዚአብሔር ሰይፍ መቅሠፍት በምድሪቱ ላይ ወርዶ የእግዚአብሔር መልአክ እስራኤልን ሁሉ ያጥፋ?’ ለላከኝ ምን እንደምመልስ ቍርጡን ንገረኝ።”

13. ዳዊትም ጋድን፣ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ መሕረቱ ታላቅ ስለ ሆነ በእግዚአብሔር እጅ መውደቅ ይሻለኛል፤ በሰው እጅስ አልውደቅ” አለ።

14. ስለዚህ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ መቅሠፍት ላከ፤ ከእስራኤልም ሰባ ሺህ ሰው ዐለቀ።

15. እንዲሁም እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፉ መልአክ ላከ፤ መልአኩ ሊያጠፋትም ሲል እግዚአብሔር አይቶ ስለሚደርሰው ጥፋት አዘነ፤ ሕዝቡን የሚያጠፋውንም መልአክ፣ “እጅህን መልስ” አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ አጠገብ ቆሞ ነበር።

16. ዳዊት ቀና ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔር መልአክ በሰማይና በምድር መካከል ቆሞ አየ፤ መልአኩም በኢየሩሳሌም ላይ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ ይዞ ነበር፤ ከዚያም ዳዊትና ሽማግሌዎቹ ማቅ እንደ ለበሱ በግምባራቸው ተደፉ።

17. ዳዊት እግዚአብሔርን፣ “ተዋጊዎቹ እንዲቈጠሩ ያዘዝሁ እኔ አይደለሁምን? ኀጢአት የሠራሁትም ሆነ የበደልሁት እኔ ነኝ፤ እነዚህ እኮ በጎች ናቸው፤ ታዲያ እነርሱ ምን አደረጉ? እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ትሁን እንጂ፣ መቅሠፍቱ በሕዝብህ ላይ አይውረድ” አለ።

18. ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ዳዊት ወጥቶ በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ላይ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራ ዘንድ እንዲነግረው ጋድን አዘዘው።

19. ዳዊትም ጋድ በእግዚአብሔር ስም በነገረው ቃል መሠረት ለመፈጸም ወጣ።

20. ኦርና ስንዴ በመውቃት ላይ ሳለ ዘወር ሲል መልአኩን አየ፤ አብረውት የነበሩት አራት ወንዶች ልጆቹም ተሸሸጉ።

21. ዳዊት ወደ እርሱ እየቀረበ መጣ፤ ኦርና ቀና ብሎ ሲመለከት፣ ዳዊትን አየው፤ ከዐውድማውም ወጥቶ መሬት ላይ ለጥ ብሎ በመደፋት ለዳዊት እጅ ነሣ።

22. ዳዊትም፣ “በሕዝቡ ላይ የወረደው መቅሠፍት እንዲወገድ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እሠራ ዘንድ ዐውድማህን ልውሰደው፤ ሙሉውን ዋጋ እከፍልሃለሁ” አለው።

23. ኦርናም ዳዊትን፣ “እንዲሁ ውሰደው፤ ጌታዬ ንጉሥ ደስ ያለውን ያድርግ፤ እነሆ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሬዎቹን፣ መውቂያ በትሮቹን ለማቀጣጠያ ዕንጨት፣ ስንዴውን ደግሞ ለእህል ቍርባን እንዲሆን እሰጣለሁ፤ ሁሉንም እኔ እሰጣለሁ።” አለ።

24. ንጉሥ ዳዊት ግን ለኦርና “አይደረግም፤ ሙሉውን ዋጋ እኔ እከፍላለሁ፤ የአንተ የሆነውን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ አልፈልግም፤ ዋጋ ያልከፈልሁበትንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አላቀርብም” ሲል መለሰለት።

25. ስለዚህ ዳዊት ለኦርና የቦታውን ዋጋ ስድስት መቶ ሰቅል ወርቅ ከፈለ።

26. ዳዊትም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠርቶ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረበ። እግዚአብሔርንም ጠራ፤ እግዚአብሔርም የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ከሰማይ በእሳት መለሰለት።

27. ከዚያም እግዚአብሔር ለመልአኩ ተናገረ፤ መልአኩም ሰይፉን ወደ አፎቱ መለሰ።

28. በዚያን ጊዜ ዳዊት፣ እግዚአብሔር በኢያቡሳዊው በኦርና ዐውድማ ላይ እንደ መለሰለት ሲያይ፣ በዚያው ቦታ መሥዋዕት ማቅረብ ጀመረ።

29. ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእግዚአብሔር ማደሪያ ድንኳንና የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያ በዚያ ጊዜ በገባዖን ኮረብታ ላይ ነበረ።

30. ዳዊት የእግዚአብሔርን መልአክ ሰይፍ ስለ ፈራ ወደዚያ ሄዶ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ አልቻለም።