ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 17:7-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. “እንግዲህ አሁንም ለባሪያዬ ለዳዊት እንዲህ ብለህ ንገረው፤ “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘የሕዝቤ የእስራኤል ገዥ እንድትሆን በጎችን ከመጠበቅና ከመከተል አንሥቼ ወሰድሁህ።

8. በሄድህበት ሁሉ ከአንተ አልተለየሁም፤ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁልህ፤ አሁንም ስምህን እንደ ምድር ታላላቅ ሰዎች ስም ገናና አደርገዋለሁ።

9. ለሕዝቤ ለእስራኤል መኖሪያ ስፍራ እሰጠዋለሁ፤ የራሳቸውም መኖሪያ ስፍራ እንዲኖራቸው ከእንግዲህም በኋላ እንዳይናወጡ አደርጋቸዋለሁ። ክፉ ሰዎች በመጀመሪያ እንዳደረጉት ሁሉ፣ ከእንግዲህ አይጨቁኗቸውም፤

10. ከዚህ ቀደም በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪዎች በሾምሁ ጊዜ ጨቋኞቹ ያደረጉትን ዛሬ አያደርጉትም፤ ጠላቶቻችሁን ሁሉ አዋርዳቸዋለሁ።“ ‘እግዚአብሔር ቤት እንደሚሠራልህ በግልጽ እነግርሃለሁ፤

11. ዘመንህን ጨርሰህ ወደ አባቶችህ በምትሄድበት ጊዜ፣ ከአብራክህ ከተከፈሉት ልጆችህ አንዱ በእግርህ እንዲተካ አደርጋለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለታለሁ፤

12. ቤት የሚሠራልኝም እርሱ ነው፤ እኔም ዙፋኑን ለዘላለም አጸናለሁ።

13. አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ጽኑ ፍቅሬን ከአንተ በፊት ከነበረው ላይ እንደወሰድሁ፣ ከእርሱ ላይ ከቶ አልወስድም።

14. በቤቴና በመንግሥቴ ላይ ለዘላለም አኖረዋለሁ፤ ዙፋኑም ለዘላለም ይጸናል።” ’

15. ናታንም የዚህን ሁሉ ራእይ ቃል ለዳዊት ነገረው።

16. ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦም እንዲህ አለ፤“እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ለመሆኑ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤተ ሰቤስ ምንድን ነው?

17. አምላክ ሆይ፤ ይህ በፊትህ በቂ እንዳልሆነ ቈጥረህ ስለ ወደፊቱ የባሪያህ ቤት ተናገርህ። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ እኔንም ከሰዎች ሁሉ እጅግ የከበረ ሰው አድርገህ ተመለከትኸኝ።

18. “ባሪያህን ስላከበርኸው፣ ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ማለት ይችላል? ባሪያህን እኮ ታውቀዋለህ፤

19. እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለ ባሪያህ ብለህና እንደ ፈቃድህም መሠረት ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ እነዚህም ታላላቅ ተስፋዎች ሁሉ እንዲታወቁ አደረግህ።

20. “አቤቱ፤ እንደ አንተ ያለ የለም፤ በጆሮአችን እንደ ሰማነው ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም’

21. ከግብፅ ተቤዥተህ እንዳወጣኸው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ ማን አለ? እነርሱ እግዚአብሔር ለራሱ ሊቤዣቸው ከምድር ሕዝቦች መካከል የመረጣቸው ናቸው፤ በሕዝብህም ፊት ታላላቅና አስፈሪ ነገሮችን በማድረግ መንግሥታትን በፊታቸው አሳደድህ።

22. ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘላለም የራስህ ሕዝብ አደረግኸው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተም አምላክ ሆንህለት።

23. “እግዚአብሔር ሆይ፤ አሁንም ስለ ባሪያህና ስለ ቤቱ የሰጠኸው ተስፋ ለዘላለም የጸና ይሁን፤ የሰጠኸውንም ተስፋ ፈጽም፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 17