ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 17:16-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦም እንዲህ አለ፤“እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ለመሆኑ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤተ ሰቤስ ምንድን ነው?

17. አምላክ ሆይ፤ ይህ በፊትህ በቂ እንዳልሆነ ቈጥረህ ስለ ወደፊቱ የባሪያህ ቤት ተናገርህ። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ እኔንም ከሰዎች ሁሉ እጅግ የከበረ ሰው አድርገህ ተመለከትኸኝ።

18. “ባሪያህን ስላከበርኸው፣ ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ማለት ይችላል? ባሪያህን እኮ ታውቀዋለህ፤

19. እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለ ባሪያህ ብለህና እንደ ፈቃድህም መሠረት ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ እነዚህም ታላላቅ ተስፋዎች ሁሉ እንዲታወቁ አደረግህ።

20. “አቤቱ፤ እንደ አንተ ያለ የለም፤ በጆሮአችን እንደ ሰማነው ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም’

21. ከግብፅ ተቤዥተህ እንዳወጣኸው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ ማን አለ? እነርሱ እግዚአብሔር ለራሱ ሊቤዣቸው ከምድር ሕዝቦች መካከል የመረጣቸው ናቸው፤ በሕዝብህም ፊት ታላላቅና አስፈሪ ነገሮችን በማድረግ መንግሥታትን በፊታቸው አሳደድህ።

22. ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘላለም የራስህ ሕዝብ አደረግኸው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተም አምላክ ሆንህለት።

23. “እግዚአብሔር ሆይ፤ አሁንም ስለ ባሪያህና ስለ ቤቱ የሰጠኸው ተስፋ ለዘላለም የጸና ይሁን፤ የሰጠኸውንም ተስፋ ፈጽም፤

24. ይህም ስምህ ጸንቶ እንዲኖርና ለዘላለምም ታላቅ እንዲሆን ነው። ከዚያም ሰዎች “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእውነት የእስራኤል አምላክ ነው!” ይላሉ፤ የባሪያህ የዳዊትም ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል።

25. “አምላኬ ሆይ፤ ቤት እንደምትሠራለት ለባሪያህ ገልጸህለታል፤ ስለዚህ ባሪያህ ወደ አንተ ለመጸለይ ድፍረት አገኘ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 17