ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዜና መዋዕል 17:10-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ከዚህ ቀደም በሕዝቤ በእስራኤል ላይ መሪዎች በሾምሁ ጊዜ ጨቋኞቹ ያደረጉትን ዛሬ አያደርጉትም፤ ጠላቶቻችሁን ሁሉ አዋርዳቸዋለሁ።“ ‘እግዚአብሔር ቤት እንደሚሠራልህ በግልጽ እነግርሃለሁ፤

11. ዘመንህን ጨርሰህ ወደ አባቶችህ በምትሄድበት ጊዜ፣ ከአብራክህ ከተከፈሉት ልጆችህ አንዱ በእግርህ እንዲተካ አደርጋለሁ፤ መንግሥቱንም አጸናለታለሁ፤

12. ቤት የሚሠራልኝም እርሱ ነው፤ እኔም ዙፋኑን ለዘላለም አጸናለሁ።

13. አባት እሆነዋለሁ፤ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ጽኑ ፍቅሬን ከአንተ በፊት ከነበረው ላይ እንደወሰድሁ፣ ከእርሱ ላይ ከቶ አልወስድም።

14. በቤቴና በመንግሥቴ ላይ ለዘላለም አኖረዋለሁ፤ ዙፋኑም ለዘላለም ይጸናል።” ’

15. ናታንም የዚህን ሁሉ ራእይ ቃል ለዳዊት ነገረው።

16. ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦም እንዲህ አለ፤“እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ለመሆኑ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤተ ሰቤስ ምንድን ነው?

17. አምላክ ሆይ፤ ይህ በፊትህ በቂ እንዳልሆነ ቈጥረህ ስለ ወደፊቱ የባሪያህ ቤት ተናገርህ። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ እኔንም ከሰዎች ሁሉ እጅግ የከበረ ሰው አድርገህ ተመለከትኸኝ።

18. “ባሪያህን ስላከበርኸው፣ ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ማለት ይችላል? ባሪያህን እኮ ታውቀዋለህ፤

19. እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለ ባሪያህ ብለህና እንደ ፈቃድህም መሠረት ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ እነዚህም ታላላቅ ተስፋዎች ሁሉ እንዲታወቁ አደረግህ።

20. “አቤቱ፤ እንደ አንተ ያለ የለም፤ በጆሮአችን እንደ ሰማነው ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለም’

21. ከግብፅ ተቤዥተህ እንዳወጣኸው እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ ማን አለ? እነርሱ እግዚአብሔር ለራሱ ሊቤዣቸው ከምድር ሕዝቦች መካከል የመረጣቸው ናቸው፤ በሕዝብህም ፊት ታላላቅና አስፈሪ ነገሮችን በማድረግ መንግሥታትን በፊታቸው አሳደድህ።

22. ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘላለም የራስህ ሕዝብ አደረግኸው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተም አምላክ ሆንህለት።

23. “እግዚአብሔር ሆይ፤ አሁንም ስለ ባሪያህና ስለ ቤቱ የሰጠኸው ተስፋ ለዘላለም የጸና ይሁን፤ የሰጠኸውንም ተስፋ ፈጽም፤

24. ይህም ስምህ ጸንቶ እንዲኖርና ለዘላለምም ታላቅ እንዲሆን ነው። ከዚያም ሰዎች “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእውነት የእስራኤል አምላክ ነው!” ይላሉ፤ የባሪያህ የዳዊትም ቤት በፊትህ የጸና ይሆናል።

25. “አምላኬ ሆይ፤ ቤት እንደምትሠራለት ለባሪያህ ገልጸህለታል፤ ስለዚህ ባሪያህ ወደ አንተ ለመጸለይ ድፍረት አገኘ።

26. እግዚአብሔር ሆይ፤ በእውነት አንተ አምላክ ነህ፤ ይህንንም መልካም ተስፋ ለባሪያህ ሰጥተሃል።

27. በፊትህ ለዘላለም እንዲኖር አሁንም የባሪያህን ቤት ልትባርክ ወደሃል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የባረክኸው አንተ ስለ ሆንህ፣ ለዘላለም የተባረከ ይሆናል።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዜና መዋዕል 17