ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ነገሥት 11:14-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. እግዚአብሔር ከኤዶም ንጉሣዊ ቤተ ሰብ ኤዶማዊውን ሃዳድን በሰሎሞን ላይ አስነሣው።

15. ከዚያ በፊት ዳዊት ከኤዶም ጋር በተዋጋ ጊዜ፣ የሞቱትን ለመቅበር መጥቶ የነበረው የሰራዊቱ አዛዥ ኢዮአብ የኤዶምን ሰዎች ሁሉ ፈጅቶ ነበር።

16. ኢዮአብና እስራኤላውያን ሁሉ፣ በኤዶም ያሉትን ወንዶች በሙሉ እስኪያጠፉ ድረስ፣ እዚያው ስድስት ወር ቈይተው ነበርና።

17. ሃዳድ ግን ገና በልጅነቱ አባቱን ካገለገሉ ጥቂት ኤዶማውያን ጋር ወደ ግብፅ ሸሸ፤

18. እነርሱም ከምድያም ተነሥተው ወደ ፋራን ሄዱ፤ ከፋራንም ሰዎች ይዘው ወደ ግብፅ በመምጣት፣ ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ፈርዖን ገቡ። ንጉሡም ለሃዳድ ቤትና መሬት ሰጠው፤ ቀለብም አዘዘለት።

19. ፈርዖንም ሃዳድን እጅግ ወደደው፤ ስለዚህም ከሚስቱ ከንግሥት ጣፍኔስ እኅት ጋር አጋባው።

20. የጣፍኔስም እኅት ጌንባት የተባለውን ልጅ ወለደችለት፤ ጣፍኔስ በፈርዖን ቤት አሳደገችው፤ ጌንባትም ከፈርዖን ልጆች ጋር አደገ።

21. ሃዳድ በግብፅ ሳለ ዳዊት ከአባቶቹ ጋር ማንቀላፋቱን፣ የሰራዊቱ አዛዥ ኢዮአብም መሞቱን ሰማ። ሃዳድም ፈርዖንን፣ “ወደ አገሬ እንድመለስ አሰናብተኝ” አለው።

22. ፈርዖንም፣ “እዚህ ምን ጐደለብህና ነው ወደ አገርህ ለመግባት የፈለግኸው?” ሲል ጠየቀው።ሃዳድም፣ “ምንም የጐደለብኝ የለም፣ ብቻ እንድሄድ ፍቀድልኝ” አለ።

23. እግዚአብሔርም ከጌታው ከሱባ ንጉሥ ኰብልሎ የነበረውን የኤልያዳን ልጅ ሬዞንን ሌላ ጠላት አድርጎ በሰሎሞን ላይ አስነሣው፤

24. ዳዊት የሱባን ኀይል በደመሰሰ ጊዜ፣ ሬዞን ሰዎቹን በዙሪያው አሰባስቦ የወንበዴ አለቃ ሆነ፤ ሰዎቹም ወደ ደማስቆ ሄደው ተቀመጡ፤ በዚያም አነገሡት።

25. ሃዳድ ካስከተለበት ችግር ሌላ ሬዞን በሰሎሞን ዘመን ሁሉ ሌላው የእስራኤል ተቃዋሚ ሆነ፤ ሬዞን ሶርያን ገዛ፤ እስራኤልንም ይጠላ ነበር።

26. እንዲሁም ከሰሎሞን ሹማምት አንዱ የሆነው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በንጉሡ ላይ ዐመፀ፤ እርሱም ከጸሬዳ የመጣ ኤፍሬማዊ ሲሆን፣ እናቱ ጽሩዓ የተባለች መበለት ነበረች።

27. በንጉሡ ላይ ያመፀበትም ምክንያት እንዲህ ነው፤ ሰሎሞን ድጋፍ የሚሆኑ እርከኖች በመሥራት የአባቱን የዳዊትን ከተማ ቅጥር ይጠግን ነበር።

28. ኢዮርብዓም ከፍተኛ ችሎታ ያለው ሰው ነበር፤ ሰሎሞንም ወጣቱ ሥራውን እንዴት በሚገባ እንደሚያከናውን ባየ ጊዜ፣ በዮሴፍ ነገድ ለሚሠራው የጒልበት ሥራ ሁሉ ኀላፊ አደረገው።

29. በዚያ ጊዜም ኢዮርብዓም ከኢየሩሳሌም ሲወጣ፣ የሴሎው ነቢይ አኪያ በመንገድ ላይ ተገናኘው፤ አኪያም አዲስ መጐናጸፊያ ለብሶ ነበር፤ ሁለቱ ብቻቸውን ሳሉ፣

30. አኪያ የለበሰውን አዲስ መጐናጸፊያ ይዞ ዐሥራ ሁለት ቦታ ቀደደው።

31. ከዚያም ኢዮርብዓምን እንዲህ አለው፤ “ዐሥሩን ቊራጭ ለራስህ ውሰድ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘እነሆ፤ መንግሥቱን ከሰሎሞን እጅ እቀዳለሁ፤ ዐሥሩን ነገድ ለአንተ እሰጣለሁ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ነገሥት 11