ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 3:2-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ዐይኖቹ ከመድከማቸው የተነሣ ማየት የተሳነው ዔሊ አንድ ሌሊት በስፍራው ተኝቶ ነበር።

3. ሳሙኤልም ደግሞ የእግዚአብሔር ታቦት ባለበት፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ተኝቶ ነበር፤ የእግዚአብሔር መብራትም ገና አልጠፋም ነበር።

4. እግዚአብሔርም ሳሙኤልን ጠራው።ሳሙኤልም፣ “እነሆኝ” አለ፤

5. ወደ ዔሊም ሮጦ በመሄድ፣ “እነሆኝ የጠራኸኝ” አለው።ዔሊ ግን፣ “እኔ አልተጣራሁም፤ ተመልሰህ ተኛ” አለው፤ እርሱም ሄዶ ተኛ።

6. ደግሞም እግዚአብሔር፣ “ሳሙኤል!” ብሎ ጠራው።ሳሙኤልም ተነሣና ወደ ዔሊ ሄዶ፣ “እነሆኝ የጠራኸኝ” አለው።ዔሊም መልሶ፣ “ልጄ ሆይ፤ እኔ አልተጣራሁም፤ ተመልሰህ ተኛ” አለው።

7. በዚያም ጊዜ ሳሙኤል እግዚአብሔርን ገና አላወቀም ነበር፤ የእግዚአብሔርም ቃል ገና አልተገለጠለትም ነበር።

8. እግዚአብሔር ሳሙኤልን ለሦስተኛ ጊዜ ጠራው፤ አሁንም ሳሙኤል ተነሥቶ ወደ ዔሊ በመሄድ፣ “እነሆኝ የጠራኸኝ” አለው።ዔሊ በዚህ ጊዜ ብላቴናውን ይጠራ የነ በረው እግዚአብሔር መሆኑን ተረዳ።

9. በዚያ ጊዜ ዔሊ ሳሙኤልን፣ “ሂድና ተኛ፤ ከእንግዲህ ቢጠራህ ግን፣ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር’ በል” አለው። ስለዚህም ሳሙኤል ወደ ስፍራው ተመልሶ ተኛ።

10. እግዚአብሔርም መጥቶ በዚያ ቆመ፤ ቀደም ሲል እንዳደረገው ሁሉ “ሳሙኤል! ሳሙኤል!” ብሎ ጠራው።ሳሙኤልም፣ “ባሪያህ ይሰማልና ተናገር” አለ።

11. እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ የሰሚውን ሁሉ ጆሮ ጭው የሚያደርግ አንድ ነገር በእስራኤል ላይ አደርጋለሁ።

12. በዚያም ቀን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በዔሊና በቤተ ሰቡ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ እፈጽማለሁ።

13. ዔሊ በሚያውቀው ኀጢአት ምክንያት በቤተ ሰቡ ላይ ለዘላለም እንደምፈርድ ነግሬው ነበር፤ ልጆቹ አስጸያፊ ነገር አድርገዋል፤ እርሱ ግን አልከለከላቸውም።

14. ስለዚህ ‘የዔሊ ቤት በደል በመሥዋዕትም ሆነ በቊርባን ፈጽሞ አይሰረይም’ ብዬ በዔሊ ቤት ላይ ምያለሁ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 3